ሀገሬ ቲቪ

ዩክሬን ቻይናን ማናገር እፈልጋልሁ አለች

ለስድስት ወራት የዘለቀው በዩክሬና ሩሲያ ጦርነት እስካሁን ከ5 ሺህ በላይ ንጹኃን ዜጎች ሕይወታቸው ያለፈ ሲኾን 12 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ ከቤታቸው ንብረታቸው እንዲሰደዱ ኾነዋል።

ሀገራቱ ዛሬም ገላጋይ ሳያገኙ እና ለግጭታቸው መፍትሔ ሳያበጁ ጦርነቱን ቀጥለውታል።

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮለድሚርዘለንስኪ ከአውሮፓ ኀብረት እስከ አፍሪካ ኀብረት በጦርነቱ ዙሪያ ውይይት ሲያደረጉ እና ሲመክሩ ቆይተዋል። የተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት መሪዎችን በተናጠል አውርተዋል።

ቢኾንም ግን ጦርነቱ መቋጫ መፍትሄ አልተገኘለትም። ዛሬም ታዲያ ዘለንስኪ ከቻይና አቻቸው ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ ጋር መወያየትን እሻለኹ ሲሊ አስታውቀዋል።

በእርግጥ የፕሬዝዳንቱ ጥያቄ ዛሬ ላይ የተጀመረ አይደለም ጦርነቱ ከተጀመረ የካቲት ወር አንስቶ ከቻይና ጋር ት ጦርነቱ እንዲቋጭ መፍትሔ ፍለጋ ላይ ውይይት እናድርግ ሲሉ ነበር።

“ከ ፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግ ጋር በቀጥታ መነጋገር እፈልጋለሁ። በእርግጥ ከአንድ ዓመት በፊት አንድ ውይይት አድርጌ ነበር” ሲሉ ዘለንስኪ ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንቱ አክለውም “በየካቲት ወር መጠነ ሰፊው ጦርነት ከተጀመረ በኋላ ከቻይና ጋር ዉይይት ለማድረግ በይፋ ጠይቀናል። ጠቃሚ ይሆናል ብዬ ባምንም ከቻይና የፈለግነውን ዓይነት ዉይይት አላደረግንም።” ብለዋል።

የሩሲያ ዋነኛ አጋር የሆነችው ቻይና ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዩክሬን የጀመርነው "ልዩ ወታደራዊ ኦፕሬሽን ነው ሲሉ የጠሩት ድርጊት አለማውገዟ እንዳሳዘናቸው ዘለንስኪ ተነግረዋል።

ምዕራባውያን ሩሲያ በዩክሬን እየፈጸምች ያለችው ወረራ ነው ሲሉ ይግለጻሉ። ቻይና በበኩሏ ኔቶ በአውሮፓ እያደረገ ያለው መስፋፋት ነው ወደ ጦርነት እንድትገባ የገፋፋት ስትል ሀሳቧን ትገልጻለች።

በኹለቱ ሀገራት ጦርነት ቻይና የጠራ አቋሟን እንዳልገለጸች ነው የሚነገረው። በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔ ሩሲያ በዩክሬን የፈጸመችው ወረራ ነው ሲሉ ሀገራት ድርጊቱን ለማውገዝ ድምጽ በሰጡበት ወቅት ቻይና ድመጸ ተሀቅቦ መኾንን ነበር የመረጠችው።

በሰኔ ወር በነበው የመሪዎች ጉባዔ የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት እንደሚያሳስባቸው እና ጦርነቱ ለሰው ልጆች ማስጠንቀቂያ ነው ሲሉ ተናግረዋል በዚሁ ንግግራቸው ላይ ግን ሥለ ጦርነቱ መቋጫ ምክረ ሀሳብ አልሰነዘሩም።

ከሩሲያ አቻቸው ፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር ከዚህ ቀደም ባደረጉት ውይይት ቻይና ለሩሲያ “ሉአላዊነትና ደህንነት” የምትሰጠውን ድጋፍ ማረጋገጣቸውን አልጀዚራ አስታውሷል።

እነዚህ ሁሉ የቻይና ውሳኔዎች ተዳምረው ቻይና በግልጽ አትናገረው እንጂ ሩሲያን ነው የምትደግፈው የሚሉ ስሞታዎች ይቀርቡባታል።

ቮለድሚር ዘለንስኪ በበኩላቸው ቻይና ከአድሎ ነጻ የኾነ አቋም ለመያዝ የምታደርገውን ጥረት እናደንቃለን ብለውል። ነገር ግን እንደ አንድ ኃያል አገር ሩሲያን መክራም ይኹን ተቆጥታ ይህን ጦርነት እንድታስቆምልን እንሻለን ሲሉ ሀሳባቸውን ገልጸዋል።

በጉዳዩ ላይ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ ከታይዋን ጋር ዳግም ወደ ተካረረ ሰጣገባውስጥ የገባቸው እና ትኩረቷን በዚህ ጉዳይ ላይ ካደረገችው ቻይና የተሰጠ ምላሽ አልነበረም።

በሙሉጌታ በላይ
2022-08-04