ሀገሬ ቲቪ

አንድ አዛውንት የነፃ ምግብ ፍለጋ መታሰርን መረጡ

ለበርካቶች ይህ ዓለም የፈተና ቦታ ናት።በመጣር እና በመልፋት የወዛቸውን ፍሬ የሚጠብቁ በርካቶች የልፋታቸውን ያህል የማያገኙባት።

ሁሌም አይሞላም፤ ማጣት እና ማግኘት በሚፈራረቁባት በዚህች ምድር የዕለት ጉርስ ፍለጋ ወዲያ ወዲህ መታተር የበርካቶች እጣ ነው።ይህ ግን በእድሜ ማምሻ፤ ሲሆን ፈተናው የበለጠ ይገዝፋል።

የገዛ ሆዳችንን መሙላት ዛሬን በልቶ ማደርር በየቦታው ለሚያባክነን ለኛ የከበደ ኑሮ ለእነዚያ ጋሼ ለምንላቸው መራቂዎቻችን የበለጠ ዳገት ይሆናል።

አሁን የምንነግራችሁ ታሪክ የማጣት ብቻም አይደለም በህሊና ሚዛን ሊዳኝ የሚገባውም ጭምር እንጂ።

ከወደ ታይላንድ አንድ የ60 ዓመት አዛውንት ሰርቀዋል ተብለው ወደ ማረሚያ ስለመወሰዳቸው ተሰምቷል። እኚህ አዛውንት ስማቸው ፊቺት ይባላል፤ ህይወት የከበዳቸው የኑሮ ሸክም ከጫንቃቸው ላይ አልራገፍ ያለባቸው እኚህ ሰው ከሰውሞኑ ወደ አንድ ሱቅ ጎራ ይላሉ።

17 የታይላንድ ገንዘብ የሚያወጡ ከሱቁ ሦስት ሳሙናዎችን አንስተው ለመውጣት ይሞክራሉ፤ አዚህ ጋር ልብ በሉ ያደረጉት መሞከር ብቻ ነው። የሱቁ ባለቤቶችም ተሯሩጠው ይይዟቸዋል።

በሱቁ በርላይ ማስጠንቀቂያዎች ተለጥፈዋል እቃ ሰርቆ የተያዘ የእቃውን 30 እጥፍ ይከፍላል፤ ሻገር ሲልም ለፖሊስ ተላልፎ ይሰጣል የሚል።

በእጃቸው የያዙትን ሳሙናዎች ተቀብለው አዛውንትነታቸው ቢያሳዝናቸው ምንም ሳያደርጓቸው ይለቋቸዋል። አዛውንቱ ፊቺት ግን አሻፈረኝ ይላሉ፤ ፖሊስ ተተርቶ ካልተያዝኩኝ በስተቀር ወዴትም አልሄድም ሲሉ።

የሱቁ ባለቤቶችም እኚህን አዛውንት ሊያግባቧቸው ይሞክራሉ፤ አዛውንቱ ግን ከሀሳባቸው ንቅንቅ አልልም ይላሉ። ለእኚህ አዛውንት ምታሰርን መምረጥ ትልቁ ምክንያት ሆድ ነው።

በቀን አንድ ግዜ እንኳ መመገብ ያቃታቸው እኚህ አዛውንት የሚያደርጉትን ያጣሉ፤ በቀን ሦስት ግዜ ለመመገብ ያላቸው አማራጭ መታሰር ብቻ እንደሆነም ያልናሉ።

አላቅማሙ ወደዚህ ሱቅ ሰተት ብለው ገብተው መያዝን መርጠዋል። የአዛውንቱ በሀሳባቸው መፅናት የሱቁን ባለቤቶች ወደ ፖሊስ እንዲደውሉ አስገደዳቸው። ፖሊስም በቦታው ደርሶ እኚህን አዛውንት ይዟቸው ሄዷል።

የአዛውንቱ ድርጊት ግን ለበርካቶ መነጋገሪያ ሆኗል፤ በታይላንድ ከግዜ ወደ ግዜ እያሻቀበ የመጣው የኑሮ ውድነት ነገር የበርካቶች ፈተና ነው። በልቶ ማደር የሰማይ ያህል የራቃቸው ዜጎች ቁጥር ከፍ ብሏል።

ታዲያ ለኚህ አዛውንት ድርጊት ተጠቂው ማን ይሆን? ወደ አፋቸው የሚያደርጉትን ቁራሽ ፍለጋ በእድሜ ፀሐይ መጥለቂያ፤ ሌባ መባልን ያስመረጣቸው ማጣት ወይስ ሌላ? ፍርዱን ለእናንተ ትተነዋል።

በሳምሶን ገድሉ
2022-08-05