ዛሬ ላይ የዓለም የሙቀት መጨመር ስለተፈጥሮ የሚገዳቸው ተመራማሪዎች እና የማህበረሰብ አንቂዎች ደጋግመው የመፍትሄ ርምጃዎችን ልንወስድበት እንደሚገባ የሚያሳስቡበት ጉዳይ ነው። ሰዎች ምድርን የያዝንበት መንገድ ለዚሁ የዓለም ሙቀት መጨመር ምክንያት ነው።
ይሄው የዓለም ሙቀት መጨመር “Global Warming” የሚለው ስያሜ ጥቅም ላይ መዋል የጀመረው በዛሬዋ ዕለት ከ46 ዓመታት በፊት ነበር። የዕለቱን ከታሪክ ትኩረት ነው።
የአየር ንብረት ለውጥ ጋር የተያያዙ ዘገባዎች፣ ጥናቶች፣ እንዲሁም ውይይቶች ላይ የማይቀር ስያሜ ነው። የዓለም ሙቀት መጨመር። ዓለም ይሄንንው ክስተት ለመቆጣጠር የምታደርገው ርምጃዋ ፍጥነት ጎሎት ፈተና ሆኗታል።
በሰው ልጆች ከባቢ ዓየርን መበከል ምክንያት የተከሰተውን ይሄንንው ደጋግመን የምንገለገልበትን የዓለም ሙቀት መጨመር ይሉት ስያሜን እንድንገለገልበት የሆነው በዛሬው ዕለት በ1965 ዓ.ም. ነበር።
ዋሌስ ስሚዝ ብሮከር የተሰኙ ተመራማሪ ነበሩ ይሄንንው ቃል ጥቅም ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ያዋሉት። በጆርናል ሳይንስ ላይ በታተመው የዓየር ንብረት ለውጥን የተመለከተው ጥናታቸው ላይ ይሄንንው ቃል በህትመቱ ዘርፍ ለመጀመሪያ ጊዜ ተጠቅመውበታል። በዚህም የዓለም ሙቀት መጨመር ጽንሰ ሃሳብ አባት ተብሎም ይጠራል።
የኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ የላሞንት ደሆርቲ የመሬት ምልከታ ተመራማሪ የሆኑት ብሮከር የዓለም የሙቀት መጨመር የሚለውን ስያሜ ከማስተዋወቃቸው አስቀድሞም የዓየር ንብረት ለውጥ ላይ የተለያዩ ዓይነት ጥናቶችን ያስተዋውቁ ነበር።
አሜሪካዊ ጂኦኬሚስት የሆኑት ብሮከር የመሬት ሙቀት በካርቦን ዳይ ኦክሳይድ የተነሳ በመጨመር ላይ ስለመሆኑ አስቀድመው ከተረዱ እና ከተነበዩ ሳይንቲስቶች አንዱ ናቸው።
በ1960 ዎቹ የዓለም ሙቀት መጨመር “Global Warming” የሚለውን ሀረግም የሳይንስ መዝገበ ቃላት ላይ ማካተት ችለዋል።
እንደተመራማሪነታቸውም ስራዎቻቸው የዓለምን ሶስት አራተኛ የሚሸፍኑት ውቅያኖሶች ላይ ያተኮረ ነበሩ። በውሃማ አካላት ኬሚስትሪ ላይ ያደረጓቸው ጥናቶችም የውቅያኖሶች ዝውውር ካርታ እና የዓየር ንብረት ጥናት ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
በጥናቶቻቸው ብዙ የመነሻ ሃሳቦችንም ለተመራማሪዎች አድርሰዋል። ብሮከር የዓለም የሙቀት መጨመር እንደዛሬው ትልቅ ስጋት ከመሆኑ ከአራት አስርት ዓመታት አስቀድሞ የበካይ ጋዞችን ልቀት እስካልቀነስን ትልቅ ፈተናዎች ውስጥ ልንገባ እንደምንችል ሲያስጠነቅቁ ነበር።
በዓየር ንብረት ጥናት ውስጥም ከሙቀት እስከ ዝናብ ሁኔታ ያሉትን ሁነቶች ስለሚወስኑት ጉዳዮችም የልየታ ጥናት አድርገው ነበር። የዓለም የሙቀት መጨመር አዝማሚያ ላይ ያደረጉት የግምገማ ጥናታቸው ዛሬም ድረስ ጠቃሚ እንደሆነ ይነገራል።
ብሮከር የዓለም ሙቀት መጨመር የሚለውን ስንሰ ሃሳብ ለሳይንሱ ዓለም ከማስተዋወቃቸው በተጨማሪ በምርምሩ ዘርፍ ላደረጉት አስተዋጽኦም የተለያዩ ሽልማቶችን አግኝተዋል።
የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮም ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የክብር ዶክትሬትን አግኝተዋል። የአየር ንብረት ሳይንስ አያት ተብሎ እስከመጠራትም ደርሰዋል።
ብሮከር የብሄራዊ ሳይንስ ሜዳሊያን በ1988 ዓ.ም. ተሸልመዋል። እኒህ የዓየር ንብረት ምርምር ላይ ለዓለም ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ሰው በ2011 ዓ.ም. በ87 ዓመታቸው አርፈዋል። ከ46 ዓመት በፊት የተነበዩት የዓለም ሙቀት መጨመር ፈተናነት ግን ዛሬም ቀጥሏል።
በአብርሃም በለጠ
2022-08-08
