ሀገሬ ቲቪ

የኬኒያ የምርጫ ውሎ

ላለፉት ወራቶች ከፍተኛ ዝግጅት እና የይምረጡኝ ቅስቀሳን ስታስተናግድ የቆየችው ኬኒያ ዛሬ ነሀሴ 03/12/2014 ዓ.ም ዜጎች ድምጽ ሲስጡ ውለዋል።

ይህ ካለፉት የኬኒያ ምርጫዎች በተለየ ከፍተኛ ወጪ የወጣበት ምርጫ ከ 22 ሚሊዮን በላይ ኬኒያውያን ቀጣይ አምስት ዓመት የሚመራቸውን ፕሬዝዳንት በዛሬው ዕለት ለምመረጥ እንደተመዘገቡ ነው የተገለጸው።

ዴቪድ ሙዋሬ፣ዊሊያም ሩቶ፣ጆርጅ ዋጃኮያ እና ራይላ ኦዲንጋ ለፕሬዝዳንትነት የሚፎካከሩ እጩዎች ናቸው።

ከነዚህ አራት ተወዳዳዎች በሀገሪቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ እና በደጋፊዎቻቸው ‘’ባባ’’ አሊያም ‘’አባቴ’’ የሚል ቅጽል ሥም የተሰጣቸው ራይላ ኦዲንጋ መሀከል ከባድ ፉክክር ሊደረግ እንደሚችልም ነው ከወዲኹ እየተነገረ የሚገኘው።

ኹለት የሥልጣን ጊዜን ተቆናጥጠው ኬኒያን ሲመሩ የነበሩትና በዚህ ምርጫ የሚሰናበቱት ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬኒያታ ለ10 ዓመት በምክትል ፕሬዝዳንትነት ሲያገልግሏቸው የነበሩትን ዊሊያም ሩቶ ትተው ወደ ራይላ ኦዲንጋ ፊታቸውን ማዞራቸው እና ድጋፍ መስጠታቸው ብዙዎችን አስገርሟል።

ፕሬዝዳንት አሁሩ ይህን ሊያደርጉ የቻሉት የ 50 ዓመት እድሜ ካላቸው ምክትላቸው ዊሊያም ሩቶ ጋር በአስተዳደር ስርዓቱ በመሀላቸው የነበረው አለመስማማት በመጉላቱ እና በመቀያየማቸው እንደኾነ ተሰምቷል።

ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በማዕከላዊ ኬንያ በምትገኘው በትውልድ ክልላቸው ኪያምቡ በሚገኝ የምርጫ ጣቢያ ድምፅ ሰጥተዋል።

“ይህ ምርጫ ነፃ እና ፍትሃዊ ይሆናል ብዬ አምናለሁ፣ የምርጫ ሂደቱ የተረጋጋ ነበር” ሲሉ ድምጽ ከሰጡ በኋላ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ዛሬ ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ ክፍት በተደረጉከ 40 ሺህ በላይ የምርጫ ጣቢያዎች የተወሰኑ የምርጫ ጣቢያዎች አንድ አይነት ያልኾኑ ድምጽ መስጫ ወረቀቶች መገኘታቸውን ተሰምቷል ይኽም ከፍተኛ ወጪ ወጥቶበታል በተባለው ምርጫው ላይ የተወሰነ ጥያቄ ማስነሳቱ አልቀረም። ይህ ችግር መፈጠሩ ከድምጽ መስጫው ወረቀት ህትመት ጋር ተያይዞ እንደኾነ የኬኒያ ምርጫ ኮሚሽ ሊቀ መንበር ዋፉላ ቼቡካቲ ተናግረዋል።

በዚህም በአራት የምርጫ ጣቢያዎች ላይ እገዳ እንደተጣለ የኬኒያን ምርጫ ኮሚሽንን ጠቅሶ ቢቢሲ የዘገበው። ሌላው በምርጫው የታየው እንከን ኬኒያ ከሶማሊያ ጋር በምትዋሰንበት በሰሜን ምስራቁ ክፍል ለመምረጥ የወጡ ዜጎችን አልሸባብ እያስፈራራቸው መኾኑ ነው። ሰኞ ምሽት የቡድኑ ታጣቂዎች ማንዴራ በተሰኘው ግዛት ባሉ መንደሮች ላይ ጥቃት አድርሶ ነበርም ተብሏል።

በአጠቃላይ የዛሬው ምርጫ ከፕሬዝዳንትነት ባለፈ ኬኒያውያን የክልል አስተዳዳሪዎቻቸውን፣ ሴናተር፣የምክር ቤት አባላትን እንዲሁም በምክር ቤቱ የሴቶች ተወካዮችን እና ሕግ አውጪዎችን ይመርጣሉ። በአጠቃላይ በዛሬው ምርጫ የኬኒያ ሕዝብ ከ16,000 በላይ የሀገሪቱን ሹማምንቶችን ይመርጣሉ ሲል አልጀዚራ ዘግቧል።

ከ383 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ለዚህ ምርጫ ወጪ መኾኑ ተሰምቷል ይህም ከፍተኛ ወጪ የወጣበት ምርጫ አድርጎታል። በዋጋ ግሽበት፣ በምግብ እና የነዳጅ ውድነት፣ በሥራ አጥነት እና በድርቅ እየተፈተነች በምትገኘው ኬኒያ ቀጣይ ስልጣን ላይ የሚወጣው ፕሬዝዳንት ከባድ የቤት ሥራ እንደሚጠብቀው ነው ከወዲሁ እየተነገረ ያለው።

ከአንድ ሳምንት በኋላ በሚገለጽው አጠቃላይ ውጤት አሸናፊ የሚኾነው እጩ በመላ ሀገሪቱ ከተሰጠዉ ድምጽ ከግማሽ በላይ ማግኘት ይኖርበትል። ምን አልባትም ኹለት ዋና ተወዳዳሪዎች እኩል ከ50% በመቶ ድምጽ ካገኙ ኬኒያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ድጋሜ ምርጫ ልታደርግ ትችላለች ።

በሙሉጌታ በላይ
2022-08-09