አቶሚክ ቦምብ የሰው ልጅ ርስ በርሱ በሚያደርገው የጦር መሳሪያ ፉክክር ከፈጠራቸው አውዳሚ ግኝቶች አንዱ ነው። በዓለም ታሪክ ገዝፎ ወደ ሚወሳው የሁለተኛው የዓለም ጦርነት በታሪክ መለስ ስንል አንድ ሁነትን እናስታውሳለን።
ሁለት የጃፓን ከተሞች በአቶሚክ ቦምብ ከፍተኛ ውድመት እንደደረሰባቸው። ናጋሳኪ ከተማ በዛሬዋ ዕለት በ1937 ዓ.ም. ነበር ይሄው ውድመት የደረሰባት።
ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ የጦርነት የበላይነትን ለማግኘት የታጠቀችውን የአቶሚክ ቦምብ መሞከር ፈልጋለች። ለዚህ ደግሞ ጃፓን ተመርጣለች። የዚህ ምክንያቱ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጃፓን ከጀርመን እና ጣሊያን ተወዳጅታ ከነአሜሪካ በተጻራሪ ቆማለች።
የአሜሪካ አቶሚክ ቦምብ በጃፓን ከተሞች ላይ የመጣል ዕቅድ መከናወን የጃፓንን ቅስም በመስበር ጃፓናውያን ያልተጠበቀ እጅ መስጠት እንዲያደርጉ አስገድዷቸዋል።
በዛሬዋ ዕለት በ1937 ዓ.ም. አሜሪካ የጃፓን ከተማ በሆነችው ናጋሳኪ ላይ የቦምብ ጥቃቱን ለሁለተኛ ጊዜ ፈጸመች። ከቀናት በፊት ሂሮሽማ ላይ የአቶሚክ ቦምብ ጥቃቱን አዝንባ ነበር።
ግና ደግሞ ለአሜሪካ የሄሮሽማ ውድመት የጃፓን ጦር ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እጁን እንዲሰጥ በቂ ሆኖ አልተገኘም። “ፋት ማን” በሚል ስያሜ የሚታወቀውን ሁለተኛውን አቶሚክ ቦምብ ለመጣል አቀደች። ይሁንና ግን ሊጣል የታሰበበት ዕለት የተተነበየው መጥፎ የዓየር ሁኔታ ሊጣል የታቀደበት ዕለትን ሁለት ቀናት ወደኋላ መመለስ አስፈላጊ ሆኖ ተገኘ።
በዚህም ምክንያት በዛሬዋ ዕለት ከ77 ዓመታት በፊት ጠዋት ላይ የጃፓኗ ከተማ ናጋሳኪ አውዳሚው ቦምብ ዘነበባት። “ቦክስካር” የተሰኘ ቢ 29 ቦምብ ጣይ አውሮፕላን ነበር አገልግሎት ላይ የዋለው። በፍሬደሪክ ቦክ አዛኝነት ከቲናይ አይስላንድ በመነሳት በማጅ ቻርለስ ስዊኒ መሪነት ነበር ናጋሳኪ ላይ ጥቃት ያደረሰው።
የመርከብ ግንባታ ማዕከል የነበረችው ናጋሳኪ ከፍተኛ ውድመት ደረሰባት። ከሶስት ቀናት አስቀድሞ የአሜሪካ ቢ 29 ቦምብ ጣይ አውሮፕላን በሌላኛዋ 350,000 ህዝብ በሚኖርባት የጃፓን ከተማ ሄሮሺማ ጥቃት ፈጽሟል።
80 ሺህ ሰዎች ለመሞታቸው ምክንያት የሆነ ውድመት አድርሷል።ናጋሳኪ በጠዋቱ ክፍለ ጊዜ ከከተማዋ 502 ሜትር ከፍታ አውዳሚው ቦምብ ተጣለባት። ከተማዋ በከባድ ንውጽውጽታ ተሞላች። የተጣለባት ቦምብ የሚምር አልሆነም።
ከተማዋን የከበቧት ኮረብታዎች ከከተማዋ ውስጥ ለነበሩት ሰዎች ምንም ማድረግ አልተቻላቸውም።በርግጥ የጉዳት መጠኑን በጥቂቱም ቢሆን እንዲቀንስ ኮረብታዎቹ አስተዋጽኦ አድርገዋል ይባልላቸዋል።
ያም አለ ይህ እሳት የዘነበባቸው የከተማዋ ነዋሪዎች የሰቆቃ ሞት መሞታቸው የግድ ነበር። የሟቾች ቁጥርም ከ60 ሺህ እስከ 80 ሺህ እንደሚደርስ ይገመታል። ትክክለኛ ቁጥሩን ለማግኘት ግን በውድመቱ የጠፉ መረጃዎች መኖራቸው ከባድ ያደርገዋል።
አሜሪካ ሌላ ውድመትን በማንሃታን የመድገም ዕቅድ ነበራት ግና ደግሞ አስፈላጊ ሆኖ አልተገኘም። የጃፓን የጦር ምክር ቤት ተከፋፈለ። ጦርነት መቀጠል የጃፓን ህዝብን መጥፋት ሊያስከትል ይችላል በሚል ጦሩ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እጁን እንዲሰጥ የጃፓን ንጉሰ ነገስት ፍቃድ ሰጡ።
የሄሮሽማ እና ናጋሳኪ ክስተት ግን ምንጊዜም በታሪክ በሃዘን ይወሳል።
በአብርሃም በለጠ
2022-08-09
