ይህ የዓለማችን አደገኛው እና አስፈሪው መንገድ ነው። ደቡብ አሜሪካ፤ ቦሊቪያ። በዚህ መንገድ በህይወት ማለፍ በመርፌ ቀዳዳ የመሽሎክን ያህል ከባድ ነው ይባልለታል።
አስፈሪው የቦሊቪያ መንገድ፤ በወል መጠሪያው የሞት መንገድ። ዓመት አልፎ ዓመት በመጣ ቁጥር ከ2 እስከ 3 መቶ ሰው በዚህ መንገድ ዓለምን ተሰናብቶ ይሄዳል።
መንገዱ ለአንዳንዶች ጀብደኝነትን የሚለማመዱበት መዝናኛ ነው፤ ለአንዳንዶች ደግሞ የእለት ጉርስ የእንጀራ ጉዳይ። እንጀራቸውን ብለው በዚያ መንገድ የሚያልፉ ሁሉ መቀበሪያቸውን እያዩ ያልፋሉ፤ በእያንዳዱ መታጠፊያ ልክ ለተጨመረላቸው እድሜ እያመሰገኑ።
ሁሉንም ግን ሞት አንድ ያደርጋቸዋል፤ መንገዱ ከአንደኛው የሀገሪቱ ጫፍ ወደሌላኛው ከማሻገር ይልቅ ወደ ማይቀርበት ዓለም ማሻገር ይቀለዋል።
ከ1991 እስከ 1995 ዓ.ም ድረስ ባለው ግዜ ውስጥ እጅግ የበዙ ቦሊቫውያን በሰላም አግባኝ ብለው ወጥተው ወደማይቀረው ዓለም ተሻግረዋል።
በ1999 ዓ.ም የቦሊቪያ መንግስት በዚህ መንገድ ሳቢያ የሚያልቁት የሀገሪቱ ዜጎች ነገር ቢያሳስበው አማራጭ መንገድን አበጅቶ ነበር።
የሞት መንገድን ከመኪና ነፃ እንዲሆን እና የብስክሌት ጋላቢ ጀብደኞች እንዲዝናኑበት በማሰብ። ከ15 ዓመታት በኋላ ታዲያ የሀገሬው መንግስት እቅድ የሰመረ ይመስላል።
ለወትሮ የሞት መናኸሪያ የነበረው ቦታ አሁን ህይወት የሚለመልምበት ሆኗል። አሁን በቦታው ላይ የሚሞት ሰው የለም፤ በተቃራኒው ግን መንፈስን በሀሴት የሚሞላ የተፈጥሮ ግርማ ለብሶ ይታያል።
በቦታው ላይ ጥናት ያደረገ አንድ የዱር እንስሳት ጥበቃ ቡድን እንዳለው በዚህ ቦታ የበነረው መንገድ ለሰው ልጆች ሞትብቻም ሳይሆን ለዱር እንስሳቱም ፈተና ሆኖ ነበር።
ቡድኑ ባደረገው ጥናት የተወሰደው እርምጃ ተፈጥሮንም ወደ ነበረበት ለመመለስ እንደረዳው አመላክተዋል። በዚህ የቀድሞ የሞት መንገድ ላይ 35 ካሜራዎችን በተለያየ ቦታ ላይ በማጥመድ 16 አጥቢ እና 94 የአዕዋፍ ዝርያዎችን ማግኘት መቻሉን ጠቁሟል።
የቡድኑ የባዮሎጂ ባለሙያ የሆኑት ጊዶ አያላ እንዲህ ይላሉ ፡-
“ለተሰራው ስራ ምስጋና ይሁን እና ዛሬ ከባድ የጭነት መኪናዎች በዚህ መንገድ አያልፉም። ብዝሃ ህይወት ወደ ነበረበት ተመልሷል። አሁን በዚህ ቦታ እንደ ሃሚንግበርድ፣ ቱካን፣ በቀቀኖች ያሉ ወፎችን ማየት ትችላለህ” ብሏል።
የሞት መንገዱ ከተዘጋ ከ10 ዓመታት በኋላ በቦታው የተቀመጡት ካሜራዎች የቦታውን ለውጥ ቁልጭ አድርገው እያሳዩ ይገኛሉ። እንስሳቱ አሁን መኖሪያቸው ተጠብቆላቸው እንደልባቸው እየሆኑ ነው።
በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወታቸውን የገበሩበት ይህ መንገድ አሁን አቧራ አይታይበትም፤ በመንገዱም የመኪኖች ጫጫታ አይሰማበትም፣ ከሰው ሰራሽ ጫጫታ የራቀ፣ ተፈጥሮ ብቻ ድምቷ ጎልቶ የሚሰማበት ሆኗል።
ተፈጥሮን ከመገዳደር ወደ ማክበር መሻገር በቦሊቪያ የሞት መንገድ።
በሳምሶን ገድሉ
2022-08-09
