በፍልስጤም መሳቅ፤ መደሰት፤ መጫወት፤ እንዲሁም መዝናናት የሚሉ ነገሮች ከጠፉ አመታቶች ተቆጥረዋል ።
ፍልስጤም አብዛኛው ጊዜዎቿን በጦርነትና በሽብር በማሳለፏ አሁን ላይ ብዙዎች ህይወታቸውን እየመሩ የሚገኙት በከፍተኛ ጭንቀትና ድርብርት ነው።
በሀገሪቱ ውስጥ የተፈጠረውን የሰላም ማጣት አዋቂዎች በተለያዩ መንገዶች ለመርሳት ቢሞክሩም በ ታዳጊ ልጆች ላይ ያመጣው የ ስነልቦና ጫና ከፍተኛ በመሆኑ የልጆች ፊት ላይ ፈገግታን ማየት ምኞት ሆኗል።
ወትሮም የጭንቀቱ መንሰኤ የሆነችው እስራኤል ባሳለፍነው ሳምንት በግዛቲቱ ላይ የፈጸመችው የአየር ድብደባ በፍልስጤማውያን ልጆች ላይ ተጨማሪ የአይምሮ ቁስለት ጥሎ አልፏል ።
እነዚህ የፍልስጤም ልጆች ካዩትና ካሳለፉት አስከፊ የመከራ ጊዜ ለመላቀቅ ከብዷቸዋል ። ይህ የልጆች ስሜት መደፍረስ ቤተስብንም የሚያደርጉትን አሳጥቷቸዋል ።
ታዲያ ይህን የህጻናኑትን ጉዳት የተመለከቱ አንዳንድ በጎ ፍቃደኞች ልጆች ከዚህ ጫና መላቀቅ የሚችሉበትን መንገድ በማሰብ ህጻናት ይሳቁ በሚል ፕሮግራሞችን ማዘጋጀት ጀምረዋል ።
የሁነቱ አዘጋጅ የሆነው አህመድ ጃርቡ ስለ ፕሮራሙ እንዲህ ይላል ።
“ህጻናቶቹ በ ዕድሜያቸው ማየት የሌለባቸውን ነገር ስላዩ ስነልቦናቸው በጣም ተጎድተዋል ። ስለዚህ እነዚህን ልጆች በማዝናናት ካሉበት ችግር ማውጣት ስላለብን አሸንጉሊቶችንና ሊጫወቱ የሚችሉበትን ነገር በማዘጋጀት ለማሳቅ እየሞከርን ነው ። ፈጣሪ ይመስገን ተሳክቶልናል ።”
የራፋ ከተማ እስራኤል በፈጸመችባት ጥቃት ሰትታመስ ነበር የከረመችው ። በወቅቱ የነበረው የ ሮኬትና የ አየር ድብደባም ብዙ ህጻናትን ያለ ወላጅ አስቀርቷል ።
በሰዐቱም 15 ህጻናትን ጨምሮ የ44 ሰወች ህይወትን ቀጥፏል። በዚህ ቦታ ለመጫወት የመጣው ታዳጊ ዝግጅቱን እንዲህ ሲል ገልጾታል ።
“አሻንጉሊቶቹ ከኛ ጋር መጥተው ስለተጫወቱ በጣም ደስ ብሎናል ። ምክንያቱም በጦርነቱ በጣም ተጨንቀን ነበር። ብዙ ጓደኞቻችንንም አጥተናል ።”
ጦርነት ከሚያጠፋው የሰው ነፍስ እንዲሁም ከሚያወድመው ንብረት በተጨማሪ በህጻናት ላይ የሚያደርሰው የስነልቦና ጫና ቀላል አለመሆኑን ፍልስጤም ማስተማሪያ ናት ።
በዮሴፍ ከበደ
2022-08-11
