በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ6 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈው ኮቪድ 19 ቫይረስ በኢትዮጵያ መገኘቱ ከታወቀ አንስቶ እስካሁን ድረስ በርካቶችን ለሞት ዳርጓል።
በሀገራችን ከ ሰባት ሺህ በላይ ዜጎች በዚሁ ቫይረስ ሕይወታቸውን ሲያጡ ከ14 ሺ በላይ የሚኾኑት በበሽታው ተይዘዋል። ይኹን እንጂ ቫይረሱን ለመከላከል ይረዳሉ የተባሉ የጥንቃቄ እርምጃዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ ችላ እየተባሉ ዛሬ ላይ ሙሉ ለሙሉ የተረሱ እና የተተዉ መስለዋል።
እኛም የወረርሽኙ ስርጭት አሁን ላይ በምን ዓይነት ኹኔታ ይገኛል የሚለውን ለመቃኘት ለርካታ የኮቪድ 19 ቫይረስ ታማሚዎች እንክብካቤ እና ሕክምና እየሰጠ ወደሚገኘው ኤካ ኮተቤ አጠቃላይ ሆስፒታል ጎራ ብለን ነበር።
በኾስፒታሉ ያገኘናቸው የሕክምና ባለሙያዎች እና ታማሚዎች ቫይረሱ አኹንም ሰዎችን ለሞት እና ለስቃይ እየዳረገ እንደኾነ ነው የነገሩን።
ዶ/ር ዳዊት ዮሐንስ በኤካ ኮተቤ አጠቃላይ ሆስፒታል ጠቅላላ ሐኪም ናቸው ባለፉት ኹለት ዓመታት በኮቪድ 19 ለተያዙ ዜጎች ሕክምና ሲሰጡ ቆይተዋል አኹንም የሕክምና አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ።
የኮቪድ 19 የጥንቃቄ እርምጃዎች በእጅጉ ችላ መባላቸውን ነግረውናል በዚህም ሳቢያ በሆስፒታሉ በርካታ ታማሚዎች በቫይረሱ ተይዘው እየመጡ ነው ብለውናል።
ሌላው በሆስፒታሉ ያገኘናቸው ወ/ሮ ገነት የተባሉ የኮቭድ 19 ቫይረስ ታማሚ ናቸው። በሕክምና ማዕከሉ ከሳምንት በላይ ክትትል ሲያደርጉ ቆይተው አሁን ላይ ማገገም መቻላቸውን ገልጽውልናል። ወ/ሮ ገነት የጥንቃቄ እርምጃዎቹን ችላ ማለቴ ለከፍተኛ ስቃይ ዳርጎኛል ሲሉ ነግረውናል።
በአጠቃላይ በኤካ ኮተቤ አጠቃላይ ሆስፒታል በነበረን ቆይታ በኮቪድ 19 ቫይረስ የሚማቅቁ ታማሚዎችን ተመልክተናል።
ከዚህ ቫይረስ ራሳችንን ለመጠበቅ በሀገራችን ቫይረሱን የመከላከል አቅምን የሚያጎለብቱ ክትባቶች መውሰድ እና ችላ የተባሉ የጥንቃቄ እርምጃዎችን ያለመሰልቸት መፈጸም ይገባል መልክታችን ነው።
በሙሉጌታ በላይ
2022-08-11
