የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ የኢትዮጵያ የውጭ እዳ በ 2 በመቶ ቀነሱን ያብራራል፡፡ መንግሥት በ2014 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ለተወሰደ ብድር ከፍተኛ ክፍያ መፈፀም ችሏል፡፡ የውጭ እዳ መጠን ባለፈው በጀት ዓመት መጠናቀቂያ ላይ ከነበረው 29 ነጥብ 52 ቢሊየን ዶላር በመስከረም ማብቂያ የ466 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር ቅናሽ ያሳየ ነው፡፡ የገንዘብ ሚኒስቴር የእዳ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ይፋ ያደረገው የ2014 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የሀገሪቱ የእዳ ሁኔታ መግለጫ እንዳነሳው በተጠቀሰው ጊዜ የሀገሪቱ የውጭ እዳ በሁለት በመቶ ቅናሽ አሳይቶል፡፡ የብድር መጠኑም 29.05 ቢሊየን ዶላር ላይ ተቀምጧል፡፡ ለዚህም ሀገሪቱ ለተወሰደ ብድር የተከፈለች የገንዘብ መጠን ከተለቀቀ አዲስ ብድር በከፍተኛ ሁኔታ መብለጡ እንደ ምክንያት ተጠቅሷል፡፡ በ2014 የመጀመሪያዎቹ 3 ወራት ኢትዮጵያ 607.51 ሚሊየን ዶላር ለተወሰደ ብድር በክፍያ መልክ አውጥታለች፡፡ ከዚህም ውስጥ 155.38 ሚሊየን ዶላሩ ለወለድ የቀረው 452.12 ሚሊየን ዶላር ደግሞ ለዋና እዳ የተከፈለ ነው፡፡ በአንፃሩ ወደ ሀገሪቱ የገባ አዲስ ብድር በአብዛኛው ከዓለም ባንክ የመጣ ሲሆን መጠኑም 137.74 ሚሊየን ዶላር ብቻ ነው፡፡ ይህ መጠን ካለፈው አምስት አመት ወዲህ ከተለቀቁ የብድር መጠኖች እጅግ አነስተኛ መሆኑን ሰነድ ያብራራል፡፡ አዲስ የተለቀቀው የብድር መጠን ሀገሪቱ በተጠቀሰው ጊዜ ከከፈለችው አንፃር የ470 ሚሊየን ዶላር ልዩነት አለው ፡፡ የውጭ እዳ መጠን በመስከረም መጨረሻ ከጥቅል ሀገራዊ ምርት(GDP) አንጻር 26.6 በመቶ ሲሆን ከጠቅላላው የመንግሥት እዳ የ 51.3 በመቶን ድርሻ ይይዛል፡፡ በተጠቀሰው ጊዜ አጠቃላይ የመንግሥት እዳ 56.65 ቢሊየን ዶላር ሲሆን ከጥቅል ሀገራዊ ምርት( (GDP) ድርሻው 52 በመቶ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ የሀገር ውስጥ የእዳ መጠን 27.6 ቢሊየን ዶላር አካባቢ ነው፡፡
በሀገሬ ቲቪ
2021-12-23
