ተፈጥሮ፤ በውበት የተሞላ አዕምሮን የሚያድስ መንፈስን በሀሴት የሚሞላ ነው። ሁሉም ግን የራሱ የተፈጠረበት ስርዓት አለው። አንደኛው አዳኝ ሌላኛ ደግሞ ታዳኝ ይሆናል።
በዚህ ስርዓት ውስጥ እራስን ጠብቆ ቀናትን ለመሻገር ሁሉም በራሱ መንገድ የተሰጠው ፀጋ ባለቤት ነው። አንዱ ከአዳኞቹ የበለጠ የመሮጥ እና የመተጣጠፍ ችሎታን የታደለ ነው፤ ሌላኛው ደግሞ ሌላ ብቻ ሁሉም በራሱ መንገድ እራሱን ይጠብቃል።
መቼም ስለ አዕዋፍት ስናስብ ያማረ ዝማሬያቸው እና ለስላሳ ላባዎቻቸው በቶሎ ወደ አዕምሯችን ይመጣል። ይህች ወፍ ሁድድ ፒቶሂዊ በመባል ትጠራለች። ላያት የተፈጥሮ ውበትን የታደለች ደስ የምታሰኝ በራሪ ፍጥረት ናት።
ነገር ግን የዚህች ወፍ መለያ መርዛማነቷ ነው። ከአዕዋፍት ወገን ብቸኛዋ መርዛማ ፍጥረት ተብላም በተመራማሪዎች ተቀምጣለች።
በ1982 ዓ.ም የወፎችን ተፈጥሮ የሚያጠናው (ኦርኒቶሎጂስቱ) ጃክ ዱምባከር በፓስፊክ ደሴት ላይ የተለዩ የአዕዋፍት ዝርያዎችን ፍለጋ ላይ ነበረ።
በመረቡ ካጠመዳቸው ወፎች መካከል በእጁ ከመረቡ ሊያወጣቸው ሲሞክር ይህችው ሁድድ ፒቶሂዊ የምትባለዋ ወፍ እራሷን ከአዳኟ ለማስጣል በጥፍሮቿ መቦጫጨር እና በመንቁሯ እጆቹን መጋት ትጀምራለች።
በዚህን ሰዓት ጃክ ዱምባከር የተቧጨረው እጁ ከልክ በላይ ቢያመው በደመነፍስ የተቧጨረ እጁን ወደ አፉ ይከታል። ወዲያውኑ የማዞር እና የመደንዘዝ ስሜቱ ከእጁ አልፎ ወደ አፉ እና ከንፈሩ ይዛመታል።
ነገሩ ግራ የሆነበት ጃክ ዱምባከር የወፏን ላባ መልሶ ወደ አፉ ያደርገዋል ከቀደመው ጋር ተመሳሳይ ስሜትን ይሰማዋል። ከዚህም በኋላ ወፏ መርዛማ ልትሆን እንደምትችል በማሰብ ምርምርን ያደርጋል።
በዚህም ይህችው ወፍ መርዛማ መሆኗ ለዓለም ይፋ ሆነ። እስካሁን ድረስ የዘርፍፉ ተመራማሪዎች በወፏ መርዛማነት ላይ ቢስማሙም የዚያች ውፍ መርዝ መነሻ ግን ዛሬም ድረስ እንቆቅልሽ እንደሆነ አለ።
ልክ እንደ እባብ እና ጊንጡ ሁሉ በአዕዋፍቱም ዓለም መርዛማ የሆነች ፍጥረት እዚያም አለች። ተፈጥሮ መቼም ተነግሮለት አያልቅም ሁሌም አዲስ ነገርን ታቀብለናለች እና።
በሳምሶን ገድሉ
2022-08-12
