ሀገሬ ቲቪ

ሁለት ውቅያኖሶችን የሚያገናኘው የፓናማ ካናል መከፈት

ሰው ሰራሽ ግዙፍ ቦዮች(ካናልስ) መከፈት የዘመናዊ ዓለምን የባህር ላይ የንግድ እና የትራንስፖርት መልክን ቀይረውታል። በአቅራቢያችን ቀይ ባህርን ከሜዲትራኒያን ባህር የሚያገናኘው የስዊዝ ቦይ ይጠቀሳል። ወደ አሜሪካ ደግሞ የፓናማ ቦይ ስሙ ይጠራል።

ይሄው ካናል አትላንቲክ ውቅያኖስን ከፓስፊክ ውቅያኖስ አገናኝቷል። ሁለት አህጉራትን የሚከፍለው ይሄው ቦይ ለባህር ላይ መጓጓዣ መስመርነት ክፍት የሆነው በዛሬዋ ዕለት ከ108 ዓመታት በፊት ነበር።የዕለቱን ከታሪክ ትኩረታችን ነው።

የአንድ ክፍለ ዘመን ዕድሜን ያስቆጠረው የአትላንቲክ እና የፓስፊክ ውቅያኖስን የሚያገናኘው የፓናማ ቦይ ለመርከብ ጉዞ ክፍት ሆኖ የተመረቀው የዩኤስ ቬስል አንኮን በተሰኘችው የጭነት እና የመጓጓዣ መርከብ ነበር።

ከ16ኛው ክፍለ ዘመን ጀመሮ በአሜሪካ አህጉር ቅኝ ገዥ በነበረችው ስፔይን በሁለቱ የአሜሪካ አህጉራት መካካእል ሰው ሰራሽ የውሃ መንገድ አስፈላጊ መሆኑ እውቅና ተሰጥቶታል።

ይሄንንው የውሃ መስመር የመክፈት ሃሳብ አሜሪካ በ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ዩኤስ አሜሪካ የኮሎምቢያ አካል በነበረው በፓናማ የባቡር መንገድ መስራቷ የውሃ መስመር የመስራት ተነሳሽነቷን ከፍ አድርጎታል።

የሰው ሰራሽ ቦይ የመስራት ሃሳቡ ሲንሸራሸር ቆይቶም ኮሎምቢያ ቦዩን የመስራት ፍቃዷን የስዊዝ ካናልን ለገነባው ለፈረንሳዊው ፈርዲናንድ ዲ ሊሴፕስ ሰጥታለች።

በ1870ዎቹ የካናሉ ስራ ተጀመረ። ግን በ1881 ዓ.ም. በቂ ባልሆነ ዕቅድ፣ የሰራተኞች መታመም እና የገንዘብ እጥረት ሳቢያ የዲ ሊሴፕስ ድርጅት የባንክ ዕዳ ውስጥ ተዘፈቀ።

ከሶስት ዓመታት በኋላ ፊሊፕ ጂን ቡኗ ቫሪላ የተሰኘው የስዊዝ ካናል ስራ ዋና ኢንጂነር የነበረው ዲፈንት የተሰኘውን የፈረንሳይ ድርጅት ሃብት ለካናል ስራው አገኘ።

በስፔይን እና አሜሪካ ጦርነት ማብቂያ ላይ አሜሪካ በአትላንቲክ እና ፓስፊክ ውቅያኖሶች መካከል የጦር እና የንግድ መርከቦችን ለማንቀሳቀስ ካናሉን መያዝ እንደሚያስፈልጋት ዩኤስ ተገንዝባለች። ለዚህም የዩኤስ ኮንግረስ ለፈረንሳይ የካናል ኝባታው ድርጅት የገንዘብ ድጋፍ ሰጥቷል።

ለገንዘብ ድጋፏም ከኮሎምብያ ጋር ባደረገችው ስምምነት ግዛቱን የመጠቀም ዋስትና የሚሰጣት ነበር። የሃይ ባኑ ቫሪላ ስምምነት ተብሎ የሚጠራውን ይሄንንው ስምምነት የዩኤስ ኮንግረስ ሲያጸድቀው የኮሎምቢያ ምክር ቤት ግን የሉዓላዊነትን የማስደፈር ስጋት ስላደረበት ሳይቀበለው ቀረ።

በምላሹ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የሆኑት ቲኦዶር ሩዝቬልት ለፓናማ የነጻነት እንቅስቃሴን እውቅና ሰጡ። በ1896 ዓ.ም. የፓናማ ተወላጆች ከኮሎምቢያ ነጻ ነን ሲሉ አወጁ። ዩኤስ ቀደም ብላ የሰራችውን እና የምታስተዳድረውን የባቡር መስመር ቆረጠች። የአሜሪካ የጦር መርከቦች ወደ ፓናማ ተጠጉ።

በዚህም የኮሎምቢያ ጦር ወደ ፓናማ መጥቶ አመጹን ለማስቆም ሳይበረታታ ቀረ። አሜሪካም ለፓናማ ሪፐብሊክ እውቅና ሰጠች። ከፓናማ ያደረገችው ስምምነትም በካናሉ ላይ ቋሚ ባለቤትነት ሰጣት።

በምላሹ ፓናማ የ10 ሚሊዮን ዶላር አግኝታለች። በርግጥ ስምምነቱን ብዙ ፓናማውያን ሉዓላዊነትን የሚጋፋ ነው ሲሉ ወዲያው ተቃውመውት ነበር።

የአሜሪካ ኢንጂነሮች የካናል ስራው ላይ ተሳትፏቸውን አሳደጉ። ከትላልቆቹ የዓለማችን የኝባታ ፕሮጀክቶቹ አንዱ የሆነውን ፓናማን የ183 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ስራን ጀመሩ። የ82 ኪ.ሜ. ርዝመት ያለውን ቦይ የ400 ሚሊዮን ዶላር ግንባታ ሰርተው አጠናቀቁ። ይሄው ካናል ታዲያ በዛሬዋ ዕለት በ1906 ዓ.ም. ነበር ለመጓጓዣ አገልግሎት ክፍት የሆነው።

ኋላም ፓናማ ከአሜሪካ ያደረገችውን ስምምነት ለመሻር ግፊት አደረገች። የፓናማው ኦማር ቶሪጆስ ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጂሚ ካርተር ጋር የፓናማ ቦይን ለማስመለስ ስምምነት አደረጉ። በስምምነታቸው መሰረት በ20ኛው ክፍለ ዘመን ማላለቂያ በ1991 ዓ.ም. ይሄው ካናል በሰላማዊ መንገድ ለፓናማ ተመለሰ።

በታሪክ ትልቅ ከሚባሉ የኢንጂነሪንግ ውጤቶች አንዱ የሆነው ፓናማ ካናል በቀን ከ40 በላይ መርከቦችን የሚያስተናግድ ሲሆን በ2021 ብቻ የ2.97 ቢሊዮን ዶላርን አስገኝቷል።

በአብርሃም በለጠ
2022-08-15