ሀገሬ ቲቪ

የኬኒያ የምርጫ ውጤት ያስከተለው ሥጋት

ከሳምንት በፊት ተካሔዶ በነበረው የኬኒያ ምርጫ በትላንትናው ዕለት አሸናፊው እጩ ይፋ ኾኗል። ለአስር አመታት የሀገሪቱ ምክትል ፕሬዝዳንት የነበሩ ዊሊያም ሩቶ የኬኒያ ፕሬዝዳንት መኾን የሚያስችላቸውን ውጤት አግኝተዋል። ከብርቱ ተፎካካሪአቸው ራይላ ኦዲንጋ ጋር በጣባብ ልዩነት ነው ሊያሸንፉ የቻሉት።

ዊሊያም ሩቶ ከአጠቃላዩ የመራጭ ድምጽ 50.49 በመቶውን ሲያገኙ ራይላ ኦዲንጋ ደግሞ 48.85 በመቶ ድምጽ አግኝተዋል።

ዊሊያም ሩቶ የኬኒያ ፕሬዝዳንት መኾናቸው ከተረጋገጠ በኋላ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ሁከት እና ረብሻ እንደተፈጠረ በርካታ የብዙኃን መገናኛዎች ዘግበዋል።

በተለይም የራይላ ኦዲንጋ ደጋፊዎች ምርጫው ውጤት ላይ ቅሬታ አለን፤ተጭበርብሯል ማለታቸውን ተከትሎ ነው ተቃውሞአቸውን መንገድ በመዝጋት እና ጎማ በማቃጠል እየገለጹ የሚገኙት።

አራት የምርጫ ኮሚሽን አባላት የውጤት ገለጻው ከግልጽነት የራቀ እንደኾነና ኃላፊነት እንደማይወስዱ በማሳወቅ ራሳቸው አግልለዋል። በምርጫ ኮሚሽን አባላት ውስጥም መከፋፈል ተፈጥሮ እንደነበር ቢቢሲ ዘግቧል።

ይሁን እንጂ ዊሊያም ሩቶ የኬኒያ ፕሬዝዳንት መኾናቸው ተረጋግጧል። እሳቸውም በዚህ ምርጫ ትልቅ አስተዋጻኦ የነበራቸውና ምስጋና የሚቸራቸው የኬኒያ ሕዝብ ነው ብለዋል በራይላ ኦዲንጋ ትችት እየቀረበበት የሚገኘውን የኬኒያን የምርጫ ኮሚሽንም ጀግናችን ነው ሲሉ አወድሰዋል።

“የኬኒያን ሕዝብ በተለይም ለምርጫው የወጣው 14 ሚሊዮን ሕዝብ ትልቁ አሸናፊ እንደኾነ መናገር እፈልጋለኹ። የዚህ ምርጫ ጀግናችን ደግሞ በዋፉላቻቡካቲ የሚመራው የምርጫ ኮሚሽን ነው”

በሚቀጥሉት አምስት የስልጣን ዓመታትም ሩቶ ከሁሉም ሰው ጋር በጋራ እንደሚሠሩ ቃል አዲሱ የኬኒያ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ተናግረዋል። ግልጽ እና ታማኝ መንገሥት እንደሚመሰርቱም ለሕዝባቸው ቃልገብተዋል።

“ግልጽ ታማኝ እና ዴሞክራሲያዊ መንግሥት እንደምመሰርት ለኬኒያውያን ቃል መግባት እፈልጋሉ። ተቃዋሚ ወገኖችም በአስተዳደሬ ላይ ቁጥጥር እስከሚያደርጉ ድረስ እስከመጨረሻሁ አብሬ እሰራለሁ”

ዊሊያም ሩቶ የኬኒያ ፕሬዝዳንት መኾናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት መሪዎች የእንኳን ደስ አሎት መልእክታቸውን እያስተላለፉ ይገኛሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዊሊያም ሩቶን እንኳን ደሳሎት በማለት በቀጣይ ሁለቱ ሀገራት በሁለትዮሽና በቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ አንድ ላይ እንሰራለን ሲሉ ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ በኬኒያ ያለው ውጥረት ዛሬም እንደቀጠለ ነው የምርጫ ኮሚሽነሩ ቼቡካቲ ግን ውጤቱ የኬንያውያን ምርጫ የሚያንጸባርቅ ነው ብለዋል።

ከተፎካካሪው ራይላ ኦዲንጋ ወገኖች ምርጫ ኮሚሽኑ በሀሳብ የተከፋፈለበትን ድምጽ እኛ አንቀበለውም ብለዋል። ራይላ ኦዲንጋ በሰባት ቀናት ውስጥ ምርጫውን እንደማይቀበሉ አስታውቀው ክስ ካልመሰረቱ ምርጫው ይጸድቃል።

በሙሉጌታ በላይ
2022-08-16