ዩዜይን ቦልት የዓለማችን የምንጊዜም ፈጣኑ ሰው ተብሎ ይጠራል። ለአጭር ርቀት ሩጫ የተፈጠረ ነውም ይባልለታል። በጀማይካ ገጠራማ ስፍራ የተወለደው ዩዜይን ቦልት ገና በ15 ዓመቱ ነበር በአጭር ርቀት ሩጫ ፍጥነቱ ዓለምን ማስደመም የጀመረው።
የ100 ሜትር የምንጊዜም ፈጣን ሰዓት 9.58 ሰከንድ ያስመዘገበው በዛሬዋ ዕለት ከ13 ዓመታት በፊት በጀርመን በርሊን ነበር። እለቱን ከታሪክ ትኩረቱን ከዚህ ላይ ያደርጋል።
በ2001 ዓ.ም. በጀርመን በርሊን የኦሎምፒክ ስቴድየም የዓለም ሻምፕዮና በመካሄድ ላይ ነው። በጊዜው የ22 ዓመቱ ዩሴይን ቦልት በውድድሩ ለመሳተፍ ተገኝቷል። የ100 ሜትር ርቀት ሩጫ ውድድር ላይ መብረቁ ቦልት ተወነጨፈ።
የዓለማችን ፈጣኑ ሰው ለመባል የበቃውን ቦልት የ100 ሜትር የዓለም ክብረ ወሰንን በእጁ አስገባ። በዚህ ርቀት ከ9.6 ሰከንዶች በታች በመግባትም የመጀመሪያው ሰው ለመባል በቅቷል። ርቀቱን ለመጨረስ የፈጀበት ጊዜ 9.58 ሰከንዶች ብቻ ነበር።
በርግጥ በ2000 ዓ.ም. በቤይጂንግ በተደረገው ኦሎምፒክ ርቀቱን ከ9.7 ሰከንዶች በታች በመግባትም የመጀመሪያው መሆን ችሎ ነበር። የቦልት ፍጥነት ዓለምን አስደምሟል።
በቤይጂንግ የወርቅ ሜዳሊያውን ቢያጠልቅም ተመልካቾች በሙሉ ፍጥነቱ እንዳልሮጠ ታዝበው ነበር። የራሱን ክብረ ወሰን ራሱ ይሰብራል የሚሉ ግምቶች ተቀምጠው ነበር። በርግጥም የራሱን ክብረ ወሰን ራሱ ሰብሮ የዓለም የፈጣኖች ፈጣን ለመሆን በቅቷል።
በሙሉ ስሙ ዩዜይን ሴንት ሊዮ ቦልት ተብሎ የሚጠራው የዓለማችን ፈጣን እግሮች ባለቤት የተወለደ በ1978 ዓ.ም. በጀማይካ በገጠራማዋ ሞንቴጎ ቤይ ነው። በጀማይካ ገጠራማ መንደር ያደገው ቦልት በልጅነቱ ለአውሮፓ እግር ኳስ ለሪያል ማድሪድ እና ማንቼስተር ዩናይትድ ልዩ ፍቅር አሳድሮ ነበር።
ነገር ግን የትምህርት ቤት አሰልጣኞቹ ወደ የመም እና የሜዳ ስፖርቶች ገፍተውታል። የመጀመሪያ ውድድሩንም በ36 ሺህ ሰዎች ፊት በጀማይካ ብሄራዊ ስቴድየም በዓለም ወጣቶች ሻምፕዮና ላይ ተሳተፈ። ገና የ15 ዓመቱ ዩሴይን ቦልት በ200 ሜትር በማሸነፍ በዕድሜ ትንሹ የርቀቱ ፈጣን የክብረ ወሰን ባለቤት ተባለ። የፈጀበት ጊዜ 19.93 ሰከንድ ነበር። ይሁንና ግን በ1996 ዓ.ም. በአቴንስ በተካሄደው ጉባኤ በጉዳት ሳቢያ ሳይሳተፍ ቀርቷል።
እንደገና ወደ ልምምድ ተመልሶ በ1999 ዓ.ም. በተካሄደው የዓለም ሻምፕዮና ላይ በ200 ሜትር የነሃስ ሜዳልያ አግኝቷል። የ100 ሜትር ርቀት ለመሮጥም አሰልጣኙ እንዲፈቅዱለት ግፊት አድርጓል። በርቀቱም የመጀመሪያ የግል ክብረ ወሰን ሰዓቱን የ10.03 ሰከንድ አስመዝግቧል።
በ2000 ዓ.ም. ደግሞ ሰዓቱን ወደ 9.76 ሰከንዶች ማሻሻል ችሏል። በዚያው ዓመት በኒው ዮርክ ከተማ ቦልት የዓለም ሪከርድን መስበር ቻለ። በዚህ ውድድር ቦልት በ9.72 ሰከንድ ርቀቱን በመጨረስ የዓለም የክብረ ወሰን ባለቤት የነበረውን ታይሰን ጋይን አሸንፎታል።
ዩሴይን ቦልት የምንጊዜም ፈጣኑ ሰው የሚለውን የክብር ስም የተጎናጸፈ ሲሆን በጀርመን በርሊን ከ13 ዓመታት በፊት የምንጊዜም ፈጣን የ100 ሜትር ክብረ ወሰን ሰዓቱን 9.58 ሰከንድ በዛሬዋ ዕለት ማስመዝገብ ችሏል።
ቀደም ብሎ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በሶስት ተከታታይ ኦሎምፒኮች በ100 ሜትር እና 200 ሜትር ርቀት የወርቅ ሜዳሊያን በማስመዝገብ የምንጊዜም የአጭር ርቀት ምርጡ ሯጭ ተደርጎ ይታሰባል።
ምንም እንኳን ዩዜይን ቦልት በ9.4 ሰከንድ 100 መትርን መጨረስ እንደሚችል ቢናገርም ከ2009 ዓ.ም. የዓለም ዋንጫ በኋላ ጡረታ ወጥቷል። ቢሆንም ግን የርቀቱ ክብረ ወሰኑ በርሱው ጸንቷል።
በአብርሃም በለጠ
2022-08-16
