እስራኤል በቀጠናው ስምምነት አለመደረሱ ዜጎቿን የማስወጣት ዕቅድ በጠቅላይ ሚስተሯ ኤርየል ሻሮን እንድትነድፍ አድርጓታል። ነዋሪዎቹ ከሚኖሩበት ስፍራ በግዴታ በቤት ለቤት አሰሳ ጭምር ነበር እንዲወጡ የተደረገው።
መካከለኛው ምስራቅ እስራኤል ተመሰርትኩ ካለች ጀምሮ ግጭቶች አላጡትም።
በ1959 ዓ.ም. የአረብ ሀገራት ከእስራኤል በገጠሙት በስድስት ቀን ጦርነት እስራኤል በአረብ ሀገራቱ ላይ በተቀዳጀችው ድል ምስራቃዊ እየሩሳሌምን፣ የጋዛ ሰርጥን እና ዌስት ባንክን ጠቅልላለች። ዜጎቿንም በቀጠናዎቹ አስፍራለች።
ለስትራቴጂ፣ ሃይማኖታዊ እና ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች ነበር ዜጎቿን በስፍራዎቹ ያሰፈረችው። ከአራት አስርት ዓመታት በኋላ ታዲያ እስራኤል ዜጎቿን ከኖሩበት ስፍራቸው ለቃችሁ ውጡ አለች። በግድም ጭምር እንዲወጡ አስገደደች።
የእስራኤል ጦር በቤት ለቤት አሰሳ ነዋሪዎቹን ከየቤቶቻቸው ማስወጣት ጀመረ። በዚህ አስገዳጅ የማስወጣት ዘመቻ አስር ሺዎችን ከጋዛ እና ዌስት ባንክ እንዲወጡ አድርጋለች። ነዋሪዎቹ ግን በተቃውሞ ጎማዎችን እስከማቃጠል ደርሰው ነበር።
በስድስቱ ቀን ጦርነት ከያዘቻቸው ግዛቶች እስራኤል በጠቅላይ ሚኒስተር ኤርዬል ሻሮን ዜጎቿን ከፍልስጤም ግዛት ማስወጣት መጀመሯ እንደ ጥሩ ጅምር ታዬ። ግና ደግሞ የእስራኤል ምድር በአምላክ ለእስራኤሎች የተሰጠ ነው ብለው የሚያምኑት እስራኤላውያን ከስፍራው ለመልቀቅ እምቢ ማለታቸው አልቀረም።
ነገር ግን ከቤቶቻቸው መውጣት ግድ ሆነባቸው። በፈቃድም በግድም ነዋሪዎቹን ከጋዛ ሰርጥ እና ከዌስት ባንክ በማውጣት ወደ እስራኤል ድንበሮች ተወሰዱ። ተልዕኮውን በመፈጸም ላይ የነበሩት ወታደሮቹ ስፍራው ባዶ እስኪሆን አንተውም ብለው ነበር።
የአስገድዶ ማስወጣቱ ከመጀመሩ አስቀድሞ ግን የእስራኤል ነዋሪዎች ለ38 ዓመታት ከቆዩባቸው የመኖሪያ ስፍራዎች ለቀው እንዲወጡ ቀነ ገደብ ተሰጥቷቸው ነበር። ቀነ ገደቡ አልቋል በሚል ነበር የማስገደድ ማስወጣቱን በዛሬዋ ዕለት በ1997 ዓ.ም. የተጀመረው።
ፍልስጤማውያን ከስፍራዎቹ የእስራኤላውያንን ማፈግፈግ በደስታ ተቀበሉት። እስራኤልም ዜጎችን ማስወጣቱን አጠናክሬ በቀናት ውስጥ አጠናቅቃለሁ አለች።
ከፍልስጤማውያን ጋር ከሚደረገው ጦርነት ከዘጠኝ ሺህ የሚልቁትን ነዋሪዎች ከቀጠናዎቹ የማራቅ ዕቅድ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማቀዳቸው እና እንደህግ በማጸደቃቸው ነበር ይሄው የተከናወነው። ግን ደግሞ የኛ ግዛት ነው ብለው በሚያምኑ እስራኤላውያን የከፋ ተቃውሞም ገጥሞታል።
40 ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ ይዛቸው ከነበሩት ስፍራዎች ነዋሪዎቿን በግዴታ ጭምር ያስወጣችው እስራኤል በስፍራው የነበሩትን የወታደሮቿን ቁጥር ግን ጨምራለች። ዜጎቿን ከጦርነት ስፍራው በካሳ ጭምር በማራቅ የመከላከያ ስፍራዋን ማጠናከር ነው ነገሩ።
ዜጎቿን ካስወጣች በኋላ እስራኤል በጋዛ የነበራትን ቁጥጥር አጠነከረች። በስፍራው የፓሌስታንያንን ምዝገባ ትቆጣጠር ጀመር። የጋዛ የውሃ እና የኤለክትሪሲቲ ብሎም የቲሌኮሚኒኬሽን አገልግሎት እስራኤል ላይ ጥገኛ እንዲሆኑ አደረገች።
በአብርሃም በለጠ
2022-08-17
