በኢትዮጵያ የተከሰተው የማዳበሪያ እጥረት ትልቅ ራስምታት ኾኖ ሳለ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ በአሲዳማነት የተጠቃ መሬት በተመሳሳይ ለግብርና ሥራው ሌላው ተግዳሮት ኾኖ ቀጥሏል። አሲዳማ መሬት ወይም አሲዳማ አፈር በአማርኛ ስያሜው የአፈር ቆምጣጣነት ይባላል።
በኢትዮጵያ መታረስ ከሚችለው 15 ሚሊዮን ሔክታር መሬት 6.5 ሚሊዮን ሔክታሩ በአሲዳማነት የተጋለጠ እንደኾነ ግብርና ሚኒስቴር ተናግሯል።
አሁን ላይ ሙሉ ለሙሉ ምርት መስጠት የማይችሉ የእርሻ መሬት መኖራቸውን በሚኒስቴሩ የአፈር ለምነት ማሻሻያ ዳይሬክተር አቶ ተፈራ ሰለሞን ገልጸዋል በዚህም ምክንያት አርሶአደሩ ከግብርናው ሥራው እየተፈናቀለ እንደኾነ ነግረውናል።
በኢትዮጵያ በአጠቃላይ ለእርሻ ሥራ ከሚውለው መሬት 43 በመቶ የሚሆነው መሬት በአሲድ የተጠቃ ነው። ከፍተኛ ዝናብ በሚያስተናግዱ ደጋ እና ወይናደጋ የሀገራችን ክፍሎች በአፈሩ ውስጥ ያለው ጠቃሚ ንጥረ ነገር በዝናብ ስለሚታጠብ እና ከአፈሩ ስለሚወጣ በዋናነት ለዚህ ችግር የተጋለጡ ናቸው።
በአፈሩ በተለይም በአራት ክልሎች ያሉ አካባቢዎች በስፋት የአፈር አሲዳማነት ተጋልጠዋል።
ከአስር ዓመት በፊት በምርታማነት መቀነስ ላይ በተደረገ ምርምር ችግሩ እንደታወቀ አቶ ተፈራ አስታውሰው፤ ይህን በምርታማነት እና በአርሶአደሩ ሕይወት ላይ ከፍተኛ ኪሳራ የሚያደርሰው የአፈር አሲዳማ መኾንን ለመከላከል በግብርና ሚኒስቴር አሲዳማ መሬትን የሚያክም ኖራ ለአርሶአደሩ እያቀረበ ነው ብለዋል።
በማዳበሪያ ዋጋ መጨመር ምክንያት በዘንድሮ በጀት ዓመት አሲዳማ መሬትን የሚያክም ኖራ ለገበሬው ማቅረብ አልተቻለም ከዚህ ባለፈ ኖራ የሚያመርቱ ተቋማት በግሉ ዘርፍ አለመኖራቸው ፍላጎት እና አቅርቦቱ ሊመጣጠን እንዳልቻለ ሰምተናል ይህ መኾኑ በግብርናው ምርታማነት ላይ የራሱን አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራልም ተብሏል።
በአሲዳማነት የተጠቃን አንድ ሔክታር መሬት ለማከም 30 ኩንታል ኖራ ያስፈልጋል።
በሙሉጌታ በላይ
2022-08-18
