ሀገሬ ቲቪ

አፄ ሚኒልክ እና እቴጌ ጣይቱ የተወለዱባት ዕለት

በጥቁሮች የመሪነት ታሪክ ውስጥ ስማቸው በጉልህ የሚወሳ ሰው ናቸው። የቅኝ ግዛት ቀንበርን የሰበሩ ህዝቦች መሪ በመሆናቸውም በታሪክ ውስጥ በደማቅ ይዘከራሉ።

የቅኝ ገዥዎችን ዕብሪት ያስተነፈሰ ህዝብ አብራክ ክፋይ የሆኑት እኒህ ሰው በቅኝ ገዥዎቹ ምዕራባውያን መገናኛ ብዙሃን ሳይቀር መወድስ ቀርቦላቸዋል።

ጥቁር አይደሉም ለማለትም ዳድቷቸዋል። እኒህ ሰው ማናቸው ካላችሁን ታዲያ አጼ ሚኒሊክ ናቸው። ወደ 1836 ዓ.ም. በታሪክ መለስ ስንል አጼ ሚኒሊክ የተወለዱት በዛሬዋ ዕለት ሆኖ እናገኘዋለን።

ባለቤታቸው እና አማካሪያቸው እቴጌ ጣይቱ ብጡልም የተወለዱት ከአራት ዓመታት ቀደም ብሎ በዚህችው ዕለት በ1832 ዓ.ም ነበር።

የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት ለማስጠበቅ፣ ሀገራችንን ከቅኝ ተገዥነት ነጻ እንድትሆን ብሎም ከከበቧት ቅኝ ገዥዎች የሚጠብቅ ወሰን ማካለልን በመምራት ስልጣኔን በሀገራችን ለማምጣት በመስራታቸው የሚወሱ መሪ ናቸው፤ አጼ ሚኒሊክ።

በዓለም ዓይንም ቢሆን ታላቁ ጥቁር እስከመባል የደረሱ እና በታላቅ አድናቆት ስማቸው የሚነሳ የሀገራችን መሪ ናቸው።

አጼ ሚኒሊክ የተወለዱት ከ178 ዓመታት በፊት በ1836 ዓ.ም. ነሐሴ 12 በሸዋ አንጎለላ ነበር። አባታቸው የጊዜው የሸዋ ንጉስ ሳህለ ሥላሴ ልጅ ኃይለ መለኮት ሲሆኑ እናታቸው ወይዘሮ እጅጋየሁ ለማ ደግሞ በንጉስ ሳህለ ሥላሴ ቤት አገልጋይ የነበሩ ናቸው።

ከንጉስ ሳህለ ስላሴ በኋላ አባታቸው ኃይለ መለኮት የሸዋ ንጉስ ሆነዋል። በሸዋ ያደጉት አጼ ሚኒልክ 11 ዓመት ሲሞላቸው በጊዜው የየስፍራውን መሳፍንት እያሸነፉ አንድ ማዕከል ያላት ኢትዮጵያን የመመስረት ዕቅድ የሰነቁት አጼ ቴዎድሮስ ወደ ሸዋ ዘምተው ሳለ የሚኒሊክ አባታቸው ኃይለ መለኮት በህመም አረፉ።

አጼ ቴዎድሮስ በሸዋ ድል ከተቀዳጁ በኋላ ሚኒልክን ከርሳቸው ጋር ይዘዋቸው ሄደዋል። ከአጼ ቴዎድሮስ ጋር በነበሩበት ጊዜም ሚኒልክ በልዩ እንክብካቤ እንዲቆዩ እና እንዲማሩ ተደርገዋል።

ከአስር ዓመታት የአጼ ቴዎድሮስ የግዞት ቆይታ በኋላ በ1857 ዓ.ም. ከሸዋና ወሎ መሳፍንት ጋር ሲጻጻፉ ቆይተው ከተከታዮቻቸው ጋር በመሆን ከመቅደላ አምልጠዋል። ወደ ሸዋ በመሄድም የሸዋ ሰው ተቀብሏቸዋል። ቀደም ብለው በአንኮበር ከተቀመጡ በኋላ ሊቼን ቆርቁረዋል።

እቴጌ ጣይቱ ብጡል ደግሞ ውልደታቸው በ1832 ዓ.ም. በበጌምድር ደብረ ታቦር ነበር። እናታቸው ወይዘሮ የውብዳር ከባለቤታቸው ደጃዝማች ብጡል ኃይለ ማርያም ከሞቱ በኋላ በጅሮንድ መዩ የተባሉትን የዓፄ ቴዎድሮስን ባለሟል አግብተው ነበር። እቴጌ ጣይቱ የቤተክርስቲያን ትምህርትን ተከታትለዋል።

ግዕዝ እንደሚያውቁ የሚነገርላቸው ጣይቱ በገናም ይጫወቱ ነበር። አጼ ሚኒሊክ በሸዋ ከነገሱ ከ12 ዓመታት በኋላ በባህርዳር አቅራቢያ የፋሲካን በዓል ሲያከብሩ በእቴጌ ጣይቱ እናት የውብዳር ቤት ተስተናግደው ነበርና በዚያው ተጫጭተው ከሁለት ዓመት በኋላ በጋብቻ ተሳስረዋል። እቴጌ ጣይቱ በአድዋ ድል ሳይቀር በአጼ ሚኒልክ ፊት ሞገስ ያላቸው አማካሪያቸው ነበሩ።

አጼ ሚኒልክ ከ1857 ዓ.ም. እስከ 1882 ዓ.ም. በሸዋ በንጉስነት ቆይተዋል። የሸዋ ንጉስ ሆነውም በዘመኑ ልማድ መሰረት ግዛታቸውን ወደ ደቡብ እና ምዕራብ አቅጣጫ ማስፋታቸው ግን አልቀረም።

ከአጼ ዮሐንስ ጋር ደግሞ የንጉሰ ነገስነት ፉክክር ውስጥ ነበሩ። እንግሊዞች በአጼ ቴዎድሮስ የታሰሩብንን ዜጎች ለማስፈታት ነው የመጣነው በሚል አጼ ቴዎድሮስን ለመውጋት ሲመጡ አጼ ዮሐንስ እገዛ አድርገውላቸው ስለነበር ከፍተኛ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ አግኝተዋል።

በዚህም ከሚኒልክ አስቀድመው ንጉሰ ነገስት ሆነዋል። ሚኒልክ የንጉሰ ነገስትነት ፍላጎት የነበራቸው ቢሆንም ከአጼ ዮሐንስ ጋር በስምምነትም በጋብቻም ለመተማመን እየተጣጣሩ ግዛታቸውን ከሸዋ ወደ ምዕራብ እና ደቡብ እያሰፉ ቆዩ።

በምዕራብ ከደርቡሾች በምስራቅ በእንግሊዞች ድጋፍ አሰብን ከያዙት ጣሊያኖች ፍጥጫ የገጠማቸው አጼ ዮሐንስ ኋላም በመተማ ከደርቡሾች ጋር ሲዋጉ በመሰዋታቸው አጼ ሚኒልክ ቀጣዩ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት ሆነዋል።

የንግስ በዓላቸው የተከናወነው በአዲስ አበባ እንጦጦ ነበር። ከ1882 ጀመሮም እስከ 1906 ዓ.ም. ንጉሰ ነገስት ሆነው ቆይተዋል።

አጼ ሚኒሊክ የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት ለማስጠበቅ ከመስራታቸው በተጨማሪም የዘመኑ ስልጣኔን ወደ ሀገራችን ለማስገባት ጥረት አድርገዋል።

ዘመናዊ ትምህርት ቤት፣ባንክ፣ ሆቴል፣ ስልክ፣ መኪና፣ ማተሚያ እና ሌሎችም የስልጣኔ ፍሬዎች ወደ ሀገራችን እንዲገቡ ለማድረግ ጥረዋል። የመጀመሪያው ጋዜጣ ‘አዕምሮ’ም ቢሆን ጅማሮው በርሳቸው ዘመን ነው።

በዘመናቸው በፍርዳቸውም ቢሆን ርትዕን በማስቀደም የሀገር አንድነት የሚጠበቅበትን፣ ግዛቷ ወደ አንድ የሚመጣበትን፣ ከሌሎች ሀገራት ጋር ያላት ግንኙነት የሚሰምርበትን እና ሀገራችንን ከከበቧት ቅኝ ገዥዎች ግዛቶቿን መጠበቅ የሚቻልበትን መንገድ ለመፍጠር ተንቀሳቅሰዋል።

አጼ ሚኒሊክ በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ በህመም ሲፈተኑ ቆይተው በ1906 ዓ.ም. አርፈዋል።

በአብርሃም በለጠ
2022-08-18