የምሽቱ ጨለማ ተወግዶ ፀሐይ ብርሃኗን ለምድር ስታቀብል፤ በማለዳው ዶሮዎች መንጋቱን ያበስራሉ። ይህ እኛ የምናውቀው ሲነገረንም ያደግንበት አባባልም፤ እውነትም ነው።
ይህ የዶሮዎች ሚና በዶሮዎቹ ዘንድ ተረስቷል የሚያሰኝ ዜናን ሰማን እና ልናጋራችሁ ወደድን። ነገሩ በጀርመን ምዕራባዊ የሀገሪቱ ክፍል ላይ የሆነ ነው።
የዶሮ ጩኸት አማሮናል ያሉት ጥንዶች ፍርድ ቤት ቆመዋል። ዶሮው ለወትሮ ከተለመደው የዶሮዎች ስርዓት ያፈነገጠ ነው ተብሎለታል።
አንዴ ጮኾ ዝም አይልም በቀን ውስጥ 200 ግዜ ድምፁን ከፍ አድርጎ ሲጮህ ይውላል። ማልዶ በ2 ሰዓት መጮህ ይጀምራል፤ ታዲያ የዚህ ዶሮ ጩኸት ማብቂያ ጀንበር ስታዘቀዝቅ ነው።
ታዲያ ይህ ሁኔታ ያማረራቸው የዶሮ አርቢው ጎረቤት የ76 ዓመቱ ፍሬድሪክ ዊልሄልም እና ሚስቱ ጁታ ጉዳዩን ፍርድ ቤት ወስደውታል።
ቤት ለሰው ልጅ ማረፊያው ነው፤ እኛ ግን በዶሮው ጩሀት ሰላማችንን አጥተናል ሲሉ ተደምጠዋል። ማረፍ ብርቅ ሆኖብኛልም ሲል ዊልሄልም ለጋዜጠኞች ተናግሯል።
ለዓመታትም ጉዳዩን በጉርብትና ባህል በሀገሬው ወግ በሰላም ለመፍታት ሞክረናል የሚሉት ጥንዶቹ አሁን ግን ከአቅማችን በላይ ሆኗል ብለዋል።
የጥንዶቹ ጠበቃ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት ከዚህ ቀደም በሌላኛው በኩል የነበረችው የዶሮ አርቢው ጎረቤት በዶሮ ጩኸት ሳቢያ ስለመሰደዷ አንስተዋል።
በድምፅ መለኪያ የተመዘነው የዚህ ዶሮ ጩኸት በማለዳ ወደ 80 ዴሲቤል እንደሚደርስ ያሳያል። ይህም ጮክ ብለው በሚያወሩ ሰዎች የተሞላ ሬስቶራንት አልያም ከፍተኛ የሆነ የትራፊክ መጨናነቅ ያለበትን ቦታ ጋር የሚወዳደር እንደማለት ነው ሲሉ ከሳሾቹ ይናገራሉ።
በሰላማዊ መንገድ መፍትሄ አጣን ያሉት ጥንዶቹ አሁን ከፍርድ ቤቱ በጎ ምላሽን ይጠብቃሉ። የዶሮው ባለቤት ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ረበሸ የተባለው ዶሮ በዶሮዎች መንጋ መካከል እንደ አለቃም የሚቆጠር ነው። ዶሮዎች የሚመራቸውን ዶሮ ይፈልጋሉ አለበለዚያ እርስ በእርስ ይጫረሳሉ ባይ ናቸው።
ለዚህም ነው ዶሮው ድምፁን ከፍ አድርጎ ቀሪዎቹን መሰሎቹን ስርዓት የሚያሲዘው። የአውራጃው ፍርድ ቤት ታዲያ የከሳሾቹንም የተከሳሽንም መከራከሪያ አድምጧል የዶሮውን ቀጣይ እጣፈንታ ለመወሰን የብይን ቀጠሮ ሰጥቷል።
በርግጥ ሰዎች በእንስሳት ላይ ሲማረሩ እና ፍርድ ቤት ሲቆሙ የመጀመሪያ አይደለም። በደቡብ ሱዳን አንድ በግ አንዲት ሴትን በግንባሩ ነርቶ ህይወቷ እንዲያልፍ በማድረጉ የሦስት ዓመት እስር እና እስሩን ሲጨርስ ለሟች ቤተሰቦች ተላልፎ እንዲሰጥ ተወስኖ እንደነበር አጫውተናቹ ነበር።
በሳምሶን ገድሉ
2022-08-18
