ከተፈጥሮ የምንቀዳው፤ አዕምሮዋችንን በሀሴት የሚሞላ ሰውነታችንን የምናክምበት መድሃኒትም ጭምር ነው። ጥበብ።
ሥነ-ስዕል ደግሞ ከእነዚህ የአዕምሮ ተፈጣሪዎች አንዱ ነው። በስዕል የሰው ልጅ ሃሳቡን፣ ተፈጥሮን የሚያይበትን መንገድ፣ ምኞቱን እና ትዝታውን ይቀልማል። ይህንን ጥበብ አምጠው የሚወልዱት ደግሞ ሰዓሊያን ናቸው።
ዛሬ ከጥበቡ ዓለም ከወደ ሥነ-ስዕሉ ጎራ እንድንል ያስገደደንን አንድ ግርምትን የሚያጭር ዜና ልናጋራችሁ ሻትን። በአንድ ግዜ 6 ስዕሎችን መሳል የምትችል ሰዓሊ እዚህ አለች መባሉን ሰማን።
ይህችው ሰዓሊ ራጃሴና ቫን ዳም ትባላለች፤ መገኛዋ ደግሞ ሮተርዳም። የ29 ዓመቷ ባለ ብሩህ አዕምሮ ሰዓሊ ሁለቱን እግሮቿን እና ሁለቱንም እጆቿን በመጠቀም በሸራዎቹ ላይ ትጠበብባቸዋለች።
ከዚህ ቀደም በሁለቱ እጆቿ ብቻ አራት የስዕል ስራዎችን በመስራት ትታወቅ እንደነበር ዴይሊ ሜይል አስነብቧል። በ16 ዓመቷ መሳል የጀመረችው አርቲስቷ ከታዋቂዎቹ ተርታ ለመሰለፍ ግዜም አልወሰደባትም።
በ2011 ዓ.ም. የበለጠ ስዕሎችን መሳል እንዳለብኝ ተሰማኝ ምክንያቱም በህመም ምክንያት ረዘም ላለ ግዜ ስዕል ሳልስል ቆይቼ ነበር የምትለው ራጃሴና ከዚያ በሁለቱም እጄ የመሳል ሀስብ መጣልኝ ትላለች።
ከድብርት ለመላቀቅም አዲስ ነገርን መሞከር ፈለኩኝ ትላለች አርቲስቷ፤ በእግሪቼም ጭምር ለመሳል ከዛም አደረኩት ማለቷን የዜና ገፁ ፅፏል።
እንዲህ ለመሳል ልምምድ ሚባል ነገር እኔጋር እይታሰብም የምትለዋ ራጃሴና አሰብኩት ከዛም አደረኩት ትላለች።
የተለያዩ ይዘት ያላቸውን ስዕሎች በአንዴ ለመሳል ሀሳብን ከአንደኛው ወደ ሌላኛው በፍጥነት መለዋወጥን ይፈልጋል ራጃሴናም ለዚህ የታደለች ናት።
በግራ እና በቀኝ አንጎሎቿ መካከል ያለው ግንኙነት ፈጣን እና ከተለመደው በሦስት እጥፍ ከፍ ያለ እንደሆነም ትናገራለች። በምስልበት ወቅት ምን አይነት ቴክኒኮችን መጠቀም እንዳለብኝ አላስበውም የምትለዋ ሰዓሊዋ በተቻለ መጠን ስዕሎቼ በትክክል እንዲታዩ ለማድረግ እሞክራለው ብላለች።
እነዚህ ውስብስብ እና የአሳሳል ቴክኒክ የበዛባቸውን ስዕሎች ለመሳል በትንሹ 40 ሰዓታትን ይፈጃል ተብሎላታል።
በሳምሶን ገድሉ
2022-08-19
