
ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የምትገነባው ሕዳሴው ግድብ የውኃ እጥረት ያስከትልብኛል በሚል ተቃውሞ ከነሱ ሀገራት መካከል ሱዳን አንዷ ናት። ይሁን እንጂ ሱዳን ስጋቷ በተቃራኒው ኾኖባት በጎርፋ አደጋ እየታመሰች ትገኛለለች ።
በተለይም በዓባይ ተፋሰስ አካባቢ ያሉ መንደሮች ሙሉ ለሙሉ በሚያስብል ደረጃ በጎርፍ አደጋ ወድመዋል። በዚህም ምክያት የዘንድሮ ክረምት ለሱዳን ጥሩ እንዳልኾነ ነው እየተነገረ የሚገኘው። በሰኔ ወር ዝናብ መጣል ከጀመረ አንስቶ በተዳጋጋሚ በተከሰተ የጎርፍ አደጋ እስካሁን ከ77 ሱዳናውያን ሕይወታቸው እናዳለፈና 14,400 መኖሪያ ቤቶች እንደወደሙ ኤቢሲ ኒወስ ዘግቧል።
ማክሰኞ ዕለት ብቻ በጎርፍ አደጋ 28 ዜጎች መጎዳታቸውን የሱዳን ብሔራዊ የሲቪል መከላከያ ምክር ቤት ቃል አቀባይ የሆኑት ብርጋዴር ጀነራል አብዱል ጃሊል አብዱል ራሒም ተናግረዋል ቃል አቀባዩ አክለውም 24 ሺህ መኖሪያ ቤቶች እና ከ 20 በላይ የመንግሥት መስሪያ ቤት ሕንፃዎች ሙሉ ለሙሉ መውደማቸውን ተነግረዋል።በሀገሪቱ በ 12 ግዛቶች በጣለው ከባድ ዝናብ ከ100 ሺህ በላይ ዜጎች የጎርፍ ተጠቂ ኾነዋል።
ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ 80 ሰዎች በጎርፋ አደጋ መሞታቸውን አፍሪካን ኒውስ በዘገባው አስታውሷል።ከኹለት ዓመት በፊት ከፍተኛ ዝናብ እና የጎርፍ አደጋ ሱዳንን እንዲሁ ሲያምሳት ነበር በወቅቱ 100 ሰዎች በዚሁ አደጋ ሕይወታቸውን ተነጥቀው ነበር በክስተቱ የተደናገጡት የሀገሪቱ ሹማምንቶች አደጋው በሚበዛባቸው አካባቢዎች ለሦስት ወራት የሚቆይ አስቸኳይ አዋጅ እንዲታወጅ አድርገው ነበር።
በዚሁ ዓመት የተመዘገበ ሌላ ጉዳይ ቢኖር ብሉ ናይል በአማርኛ ስያሜው ጥቁር አባይ በ 100 ዓመት ውስጥ ከፍተኛው ነው የተባለውን መጠን ያስመዘገበት ዓመት ነበር 17.5 ሜትር ከፍ ብሎ ሲፈስ እንደነበር ነው መረጃዎች የሚጠቁሙት። ይኽው ወንዝ ከልክ በላይ በመሙላቱ 27 ሺህ የጤና ተቋማትን አውድሞ ነበር።
በዘንድሮ ዓመትም ሱዳን ከዚሁ ችግር ልታመልጥ አልቻለችም በአንድ ጎኗ መፍትሔ በታጣለት ሕዝባዊ አመጽ ስትናጥ በሌላ ጎኗ ደግሞ በጎርፍ አደጋ እየተንገላታች ነው።
በያዝነው የክረምት ወር በስፋት ለጎርፋ አደጋ ከተጋለጡ አካባቢዎች ውስጥ ሰሜንና ደቡብ ኮርዶፋ፣ ገዚራ፣ ደቡብ ዳርፉር በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው።
አልጀዚራ የጎርፍ አደጋ በደረሰባቸው አካባቢዎች ያናገራቸው ነዋሪዎች ሕይወታችንን ከማትረፍ ውጪ ማድረግ የቻልነው ነገር የለም ብለዋል፤ መኖሪያ ቤታቸውም ሙሉ ለሙሉ እንደወደመባቸው ነው የተናገሩት።
“እዛጋ ሁለት መኝታ ቤት ነበር በዚያ በኩል ደግሞ እንዲሁ ሁለት መኝታ ቤት እና ኩሽና ነበር ከአንድ ሰዓት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ቤቱን ደረመሰው የነበረንን አንዲት ንብረት እንኳን ይዞ የመውጣት ዕድሉ አልነበረንም። ሰዎች በሕይወት መውጣታቸው ላይ ነበር ትኩረታችንን ያደረነው”
በሱዳን ውድመት እና የሰውን ሕይወት እየቀጠፈ የሚገኘው የጎርፍ አደጋ ሌላ ተደራቢ ችግር ፈጥሯል። የአደጋው ሰለባ የኾኑ ዜጎች በሚገባ የሕክምና አገልግሎት እና መጠለያ እንዲሁም ንጹህ የመጠጥ ውኃ ማግኘት እንዳልቻሉ ነው የሚናገሩት።
“ንጹህ የመጠጥ ውኃ ኾነ የሕክምና ተቋም ማግኘት አልቻልምን። ሴት ልጄ ታማ እዚህ አካባቢ ባለ ድንኳን ውስጥ ነው ያለችው። እኛ የምንችለውን ለመታደግ እየሞከርን ነው ነገር ግን ምንም አይነት የሕክምና አገልግሎት የለም”
በምሥራቃዊ ሱዳንና በኮርዶፋን ግዛቶች ከ136,000 የሚበልጡ ሰዎች በጎርፍ መጎዳታቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ ኦቻ አረጋግጧል።
በቀጣይም ቢኾን የዝናብ መጠኑ እየጨመረ ስለሚሔድ በዚያው መጠን ጉዳት ሊድርስባቸው የሚችሉ ዜጎች ሊኖሩ ይችላሉ ሲል ትንበያውን አስታውቋል።
በሙሉጌታ በላይ
2022-08-19