ሀገሬ ቲቪ

የኬንያ የነጻነት አባት ጆሞ ኬንያታ ነጻነት

ጆሞ ኬንያታ ለኬንያ ነጻነት ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። የኬንያ የነጻነት አባትም ተብለው ይታወቃሉ። ኬንያታ ለነጻነት ባደረጉት ማነሳሳት ምክንያትም በእንግሊዝ ቅኝ ገዥ ባለስልጣናት ለዘጠኝ ዓመታት በእስር እንዲቆዩ ተደርገዋል።

እኒህ ሰው ታዲያ ከእስር ነጻ እንዲሆኑ የተደረገው በዛሬዋ ዕለት ከ61 ዓመታት በፊት ነበር። ኋላም ጆሞ ኬንያታ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስተር ሆነዋል። በዕለቱን ከታሪክ እናተኩርበታለን።

ወደ 20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ መለስ ብለን የጎረቤት ሀገር ኬንያ የነጻነት አባት ጋር የተያያዘ ታሪክን እንዳስሳለን። የእንግሊዝ ቅኝ ገዥ ባለስልጣናት አንድ ለኬንያ ነጻነት የታገሉ ሰውን አስረዋል፤ጆሞ ኬንያታን።

ከዘጠኝ ዓመታት የእስር ቆይታ በኋላ ኬንያታ በ1953 ዓ.ም. በዛሬዋ ዕለት ከእስር ተፈቱ። ከኬንያታ ሁለት ዓመታት በኋላም ኬንያ ነጻ ወጣች። የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስተርም ጆሞ ኬንያታ ሆኑ። በፓን አፍሪካኒዝም ተሳትፏቸው የሚታወቁት ጆሞ ኬንያታ በሀገሪቱ የነበሩ ነጮችም ቢሆኑ በይቅርታ እንዲኖሩ ማድረግ ችለዋል።

ኬንያታ በምስራቅ አፍሪካ ከፍተኛ ቦታዎች በማውንት ኬንያ በ1880ዎቹ ነው የተወለዱት። በኬንያ ትልቁ የኩኩዩ ማህበረሰብ አባል ናቸው። በሚሽነሪዎች ተምረዋል። በ1910ሮቹ መጀመሪያ ኬንያ የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ሆነች።

ኬንያታ ደግሞ በቅኝ ገዥዎቿ ማዕከል ናይሮቢ እየኖሩ ነው። ጆሞ ኬንያታ በፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴዎች ላይ መሳተፍ ጀመረዋል። ኋላም በ1920 ዓ.ም. የኩኩዩ ሴንትራል አሶሽየሽን ዋና ጸሐፊ ሆነው ተሾሙ።

ማህበሩ የአውሮፓ ሰፋሪዎችን የጎሳውን መሬት ያላግባብ መያዝ የሚቃወም ነበር። ኋላም ወደ ቅኝ ገዥዋ ሀገር እንግሊዝ ለንደን የቅኝ ግዛት ፖሊሲን ለመቃወም ሄደዋል። ነገር ግን ባለስልጣናቱ ሊያገኟቸው ፈቃደኛ አልሆኑም።

ጆሞ ኬንያታ ወደ ለንደን ደጋግመው ተመላልሰዋል። መመላለሳቸውም ስለአፍሪካውያን መብት ቅሬታቸውን ለማቅረብ ነበር። በ1920ዎቹ በአውሮፓ በመቆየትም መደበኛ ትምህርትን የሞስኮ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ በተለያዩ ተቋማት ተከታትለዋል።

ኋላም ፌሲንግ ማውንት ኬንያ (Facing Mount Kenya) የተሰኘውን ስለኩኩዩ ማህበረሰብ እና በቅኝ ግዛት አስተዳደሩ ስለተጋፈጡት ችግር የሚያወሳ ስራቸውን አሳትመዋል። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በእንግሊዝ በማስተማር እና በመጻፍ አሳልፈዋል።

በ1930ዎቹ መጨረሻ ወደ ኬንያ የተመለሱት ኬንያታ አዲስ የተቋቋመው የኬንያ አፍሪካ ዩንየን(KAU) ፕሬዝዳንት ሆነው ተመርጠዋል። የብዙሃኑ ድምጽ ህግ ይሁን ለሚል የጸረ አመጽ እንቅስቃሴ ግፊት አድርገዋል። ሆኖም ግን ነጭ ሰፋሪዎች በቅኝ ግዛት አስተዳደሩ የጥቁሮችን ተሳትፍ ለመቀበል አሻፈረኝ አሉ።

በ1944 ዓ.ም. ማኡ ማኡ የተሰኘው የኩኩዩ ቡድን የደፈጣ ውጊያ በነጭ ሰፋሪዎች ላይ ጀመረ። ይሄው ሁነት ወደ ደም መፋሰስ እና ፖለቲካዊ ብጥብጥ አመራ። በአስር ሺህ የሚቆጠሩ ኩኩዮዎች ወደእስር ካምፖች ተወሰዱ።

ኬንያታ በአመጹ የነበራቸው ተሳትፎ ጥቂት የነበረ ቢሆንም በእንግሊዝ በመዘለፍ ከሌሎች አምስት የኬንያ አፍሪካ ዩንዬን መሪዎች ጋር የማኡ ማኡ የሽብር አመጽን በማስተዳደር በሚል ለፍርድ ቀረቡ። ንጹንነታቸውን እና የጸረ አመጽ እንቅስቃሴ ደጋፊ መሆናቸውን ቢከራከሩም ጥፋተኛ ተብለው የሰባት አመት ብይን ተሰጠባቸው።

ኬንያታ ለዓመታት ከታሰሩ በኋላ እንግሊዝ ቀስ በቀስ ኬንያን ወደ ጥቁር የብዙሃን አስተዳደር እየለቀቀች ነው። ኬንያታ በሌሉበት የኬንያ አፍሪካን ናሽናል ዩንየን(KANU) ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ።

ፓርቲው ኬንያታ እስካልተፈቱ በየትኛውም የመንግስት እንቅስቃሴ ውስጥ አልሳተፍምም አለ። ኬንያታ ከዘጠኝ ዓመታት የእስር ቆይታ በኋላ ነጻ ወጡ። ወደ ለንደን በመሄድ ስለኬንያ ነጻነት ከተደራደሩ በኋላ ኬንያ ነጻ ወጥታለች። ኬንያታም ፕሬዝዳንቷ ሆነዋል። የነጭ ሰፋሪዎችን መብት ለመጠበቅም ቃል ገብተዋል።

የቀለም እና ጎሳ ልዩነቶችን በማቻቻል ከምዕራባውያኑ ያልቸውን ፖሊሲም የተሻለ በማድረግ ኬንያ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እንድትሆን እና መረጋጋት እንዲኖራትም ሰርተዋል። በአፍሪካዊ እንቅስቃሴዎችም ተጽዕኖ ፈጣሪ ነበሩ።

በ1970 ዓ.ም. እስኪያርፉም ኬንያን በጠቅላይ ሚኒስተርነት ኋላም በፕሬዝዳንትነት አገልግለዋል።

በአብርሃም በለጠ
2022-08-22