ሀገሬ ቲቪ

8 ወር ሙሉ ያልታወቀው የሀሰት ፖሊስ ጣቢያ

የሀገሬው ሰው በጠባይ አልሰማ ያለው ቀበኛውን በህግ አምላክ ሲል ዳኛውን ህግ ያደርጋል። ይህም ተስፋውን በህግ እና በህግ አስጠባቂው ላይ ቢያደርግ ነውና ነው።

ታዲያ ይዳኘኛል ብለው፣ ለደህንነቶ ጠበቃ ያደረጊት ፖሊስም ጣቢያውም የሀሰት ነበር ቢባሉስ።

በህንዷ ቢሃር ግዛት እንዲህ ሆነ። ለስምንት ወራት የግዛቲቱ ሰዎች ፖሊስ ጣቢያ ነው ብለው ብሶታቸውንም ወንጀለኛውንም ሲያቀብሉት የነበረው ጣቢያ የሀሰት ጣቢያ ነው ተብሏል።

ነገሩን አግራሞት አንዲያጭር ያደረገው ደግሞ እውነተኛው ፖሊስ ጣቢያ እና እውነተኞቹ ፖሊሶች በዚሁ የሀሰት ነው ከተባለው ጣቢያ ትንሽ ፈቀቅ ብለው መገኘታቸው ነው።

በህንድ ፖሊስ አልያም ወታደር በማስመሰል የሚፈፀሙ ወንጀሎች የተለመዱ አይደሉም። እነዚህ 6 ሰዎች ታዲያ የሀሰት ፖሊስ መምሰል ብቻም አይደለም የሀሰት የሆነ ፖሊስ ጣቢያን በመክፈት የአካባቢውን ሰው ሲያስጨንቁት ነበር ነው የተባለው።

ከትክክለኛው ፖሊስ ጣቢያ ከመቶዎች ባልዘለለ ርቀት ላይ ተቀምጠው ከነዋሪው ጉቦ ሲቀበሉ እንደነበር ዴይሊሜይል አስነብቧል።

እነዚሁ ወንጀለኞች ፖሊስን ባስመሰሉባቸው ግዜያት ሁሉ ፖሊስ የሚሰራቸውን ስራዎች በጠቅላላ ሲከውኑ ነበር ነው የትባለው።

ወንጀለኞችን መያዝ እና ማሰር፣ እቃዎችን በኤግዚቢትነት መያዝ እና በህንድ የፖሊስ አባላት የሚታሙበትን ጉቦ መቀበል። ብቻ ምን አለፋዎት የቀራቸው ነገር የለም።

የተያዘው ወንጀል እና ማጭበርበር ነው እና ደግ ቀን ከአንድ ትክክለኛ የፖሊስ አዛዥ አይን ውስጥ አስገባቸው።

ይህ ትክክለኛ ፖሊስ ሦስት የሀሰት ፖሶችን በአንድ የገበያ አዳራሽ ሕንፃ ላይ የሚገኙ የሱቅ ባለቤቶችን ካስፈራሩ በኋላ ወደ ሀሰት ጣቢያቸው ሲያቀኑ ይመለከታል፤ ከሀሰት ፖሊሶቹ መካከል አንደኛው የያዘውን ሽጉጥ በአትኩሮት ይመለከታል።

ትክክለኛ ሽጉጥ አልነበረም፣ ለመጫውቻ የተሰራ እንጂ። ነገሩ ግራ የሆነበት ይህ ፖሊስ ታዲያ አስመሳዮቹን ጠርቶ ያናግራቸዋል፤ በየትኛው ጣቢያ ውስጥ እንደሚሰሩም ጭምር ይጠይቃቸዋል።

መልሳቸው ብዙም አልጣመውም ከዚያም እሱ ወደሚያውቀው ትክክለኛው ፖሊስ ጣቢያ ይዟቸው ይሄዳል።

እንደፖሊስ ለብሰው እንደ ፖሊስ ሲተውኑ የነበሩት አጭበርባሪዎች ታዲያ ፖሊስ አለመሆናቸውን እና የውሸት ጣቢያ ከፍተው እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ያምናሉ።

ፖሊስም ግዜ አላጠፋም ፈጥኖ የተባለውን ቦታ ከቦ ወደውስጥ ሲዘልቅ፤ ሎእሎች ሦስት የድርጊቱ ተባባሪዎችን በውስጡ ያገኛቸዋል።

ታዲያ እነዚሁ ፖሊስ ነን ባዮች አሁንም ለፖሊስ እንደሚሰሩ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል። ይህንን ሁሉ አቀነባብሯል የተባለው ሰው አሁንም በህንድ ፖሊሶች እየተፈለገ ይገኛል።

መቼም ለፍቶ በወዝ ማግኘትን የመሰለ ነገር የለም፤ ሁሌም አቋራጭ መንገዶች መጨረሻቸውም አጭር ነውና።

በሳምሶን ገድሉ
2022-08-23