አፍሪካውያን ላይ ከተፈጸሙ ግፎች የከፋው ነው። አትላንቲክን የሚያቋርጠው የባሪያ ንግድ። አራት ክፍለ ዘመናትን በፈጀው ግፍ 12 ሚሊዮን የሚደርሱ አፍሪካውያን በአትላንቲክ ውቅያኖስ ወደ አሜሪካ እንዲጓጓዙ ተደርገዋል።
ዛሬ ላይ አፍሪካ በባሪያ ንግድ ላጣችው ኪሳራ ከአውሮፓውያን ካሳ ይገባታል የሚሉ ጥያቄዎች ሁሉ ይነሳሉ። የዛሬዋ ዕለት ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ በዩኤን የባሪያ ንግድ የሚታሰብባት ቀን ነች። እኛም በዕለቱን ከታሪክ ከዚህ ላይ እናተኩራለን።
አውሮፓውያኑ ጨለማው አህጉር እያሉ የሚጠሩትን አህጉር አፍሪካ ከዳሩ ወደ መሃሉ መንደርደር ጀምረዋል። አህጉሩ በሀብት የታደለ ነው። ተፈጥሮ ሳትሰስት ቸረዋለች። የሰው ኃይልም ቢሆን በገፍ አለው።
ገና በ15ተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሺያ የፖርቹጋል መርከቦች ከአፍሪካ ባሪያ የተባሉ ሰዎችን ማጓጓዝ ጀምረዋል። ወደ ካሪቢያን። ከአፍሪካ የወሰዷቸውን ሰዎች በኬፕ ቨርዴ እና ማዴራ ደሴቶች ለስኳር ምርት እርሻ ያሰማሯቸዋል።
ለክፍለ ዘመንም የፖርቹጋል ነጋዴዎች የባሪያ ንግዱ ላይ ቀዳሚነቱን ወስደዋል። ኮንጎ እና አንጎላን ለምዕራብ አፍሪካ ጠረፍ ማዘዋወሪያ ማዕከልነት ይጠቀሟቸውም ነበር።
ኋላም በ17ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ የጀርመን፣ እንግሊዝ እና ፈረንሳይ ነጋዴዎች ሰዎችን በባርነት የመነገድ ድርጊቱ ላይ ተሳታፊ ሆኑ። የምዕራብ አፍሪካን የሰው ጭነት መጫኛቸው አደረጉት።
ከተለያዩ የአፍሪካ ክፍሎች ሰዎች በገፍ ይጋዛሉ። ከኣውሮፓውያኑ የሚያናግዱ አፍሪካውያንም መኖራቸው የሚካድ ባይሆንም ሚሊዮኖች አፍሪካውያንን በባርነት ስም በግፍ ወደ አሜሪካ አጓጓዙ።
አውሮፓውያኑ ሲሻቸው የባሪያ ንግዱ ላይ ስምምነት ያደርጋሉ። ሲሻቸው እንደመሰላቸው ያደርጉታል። ሆኖም ከነጋዴዎች ባሻገር የመንግስታት ድጋፍ ያለው የክፍለ ዘመናት ንግድ ሆኖ አልፏል።
ከአውሮፓ የጦር መሳሪያ፣ ጨርቃ ጨርቅ እና ወይን ወደ አፍሪካ ይመጣል። ባሪያ ያሏቸውን ሰዎች ለሚሸጡ አፍሪካውያን። ወደ አሜሪካ የአፍሪካ ሰዎች በባርነት ይወሰዳሉ። አፍሪካውያኑ ያመረቱት ስኳር፣ ትምባሆ እና የግብርና ምርቶች ደግሞ ከአሜሪካ ወደ አውሮፓ ይጓጓዛል።
የአትላንቲክ ውቅያኖስን የሚያቋርጠው አፍሪካውያኑን የማዘዋወሩ ስራ ግን ጥንቃቄ የጎደለው ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ለተለያየ ስቃይ ከመዳረጋቸው በተጨማሪ ወደ ውቅያኖስ የመጣል እጣ የሚደርሳቸውም ነበሩ።
እስከ 16ኛው ክፍለ ዘመን የተጓጓዙት የአፍሪካውያን ቁጥር በጥቂት 100 ሺዎች የሚቆጠር የነበረ ሲሆን ከ17ኛው ክፍለ ዘመን በኋላ የስኳር ምርት ፍላጎት መጨመሩ ወደ አሜሪካ የሚጓጓዙት አፍሪካውያን እንዲጨምሩም ምክንያት ሆኗል።
አፍሪካ ላይ የኢኮኖሚ እድገት እንዳይኖር የጎሳ ግጭቶች ባሪያ ለመማረክ እንዲስፋፉ የጦርነት ጌቶች እንዲበዙ ሴቶች እና አፍላ ልጆች እንዲማረኩ በባሪያ ስም እንዲሸጡ ምክንያት ሆኗል። የግብርና ምርትም ቢሆን በጦርነቶች ሳቢያ እንዳያድጉ ሰብብ ሆኗል። በተለይም ምዕራብ አፍሪካ በዚህ ሳቢያ ክፉኛ ተጎድቷል።
የማጓጓዝ ሂደቱም ቢሆን የአትላንቲክ ውቅያኖስን ለማቋረጥ ከጥቂት ሳምንታት እስከ ወራት የሚፈጅ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ርስ በርስ ተሳስረው እንዲጓዙ በሚደረጉት እና መርከቦቹ ከሚችሉት መጠን በላይ የሚታጨቁት አፍሪካውያን ላይ የጤና እክል እና ሞት መድረሱም የማይቀር ነበር።
ለአራት መቶ ዓመታት የቆየው ይሄው የአፍሪካውያን ላይ ግፍ በ18ኛው ክፍለ ዘመን ማብቂያ ጠንከር ያሉ ተቃውሞዎች ከወደ አሜሪካ ገጥመዋታል። የአሜሪካ የርስ በርስ ጦርነትም ሰሜነኛው የአብራሃም ሊንከን ጎራ ባርነትን የሚቃወም ነበር። አሜሪካ የባርነት ተቀባይ መሆን የለባትም የሚል አቋም ነበረው።
19ኛው ክፍለ ዘመን ለባርነት መቀጠል ምቹ ሆኖ አልተገኘም። ተቃውሞዎች በርክተዋል። ዩኤስ በህግ ከከለከለችው በኋላ እንግሊዝም በቅኝ ግዛት አስተዳደሮቿ ባርነትን ከልክላለች።
ባርነትን በመቃወሙ ረገድ ዛሬ ላይ በሃይቲ እና ዶሚኒካን ሪፐብሊክ በሚባሉት በሳንቶ ዶሚኒጎ በዛሬዋ ዕለት በ1783 ዓ.ም. የተነሳው ተቃውሞ በ18ኛው ክፍለ ዘመን ማብቂያ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
በአካባቢው የነበረው በባርነት ላይ አመጽ ትልቅ የባሪያ ንግድ መዳረሻ የነበሩት ካሪቢያን የቅኝ ግዛት ስርዓትንም አዳክሟል። ተቃውሟቸውም ደሴቷ ሃይቲ ነጻ እንድትሆን ምክንያት ሆኗል።
የባሪያ ንግድን በዛሬዋ ዕለት ማሰብን በ1989 ዓ.ም. ዩኔስኮ ጀምሯል። በ1990 ዓ.ም. የካሪቢያን ደሴቷ ሃይቲ በዓመቱ ደግሞ ሴኔጋል አስበውታል። ዛሬም በተለያዩ ዝግጅቶች በያመቱ በዩኤን ይታሰባል።
በአብርሃም በለጠ
2022-08-23
