
በአፍሪካ አሁን ያለው ድርቅ ገና ጋብ ሳይል የንጹህ ውሃ እጦት አህጉሪቱን ስጋት ላይ ጥሏታል። ናይጄሪያን ጨምሮ ስምንት ሀገራትን የሚያካልለው በሳህል አካባቢ ያለው ረሀብ ከቀን ቀን ከፍተኛ ስጋት አሳድሯል።
በአፍሪካ ቀንድም ማለትም ኬንያ፣ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ እንዲሁ በ40 ዓመታት ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ የከፋ ድርቅ ተከስቷል ።
በአፍሪካ ቀንድ እና በሳህል አካባቢ ሀገራት የተከሰተው አደገኛ ድርቅ ዋነኛ ሰበብ የዝናብ እጥረት መሆኑ ተሰምቷል። የዓለም ምግብ ፕሮግራም መረጃ እንደሚለው በምስራቅ አፍሪካም 22 ሚሊዮን የሚያህሉ ሰዎች ለረሃብ የተጋለጡ ናቸው።
የተባበሩት መንግስታት የሰበአዊ እርዳታዎች ማስተባበሪያ ቢሮ ኦቻ እንደሚገምተው በሳህል አካባቢ በየዓመቱ እድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ 600 ሺሕ ህፃናት ይሞታሉ። ከነዚህም መካከል ግማሽ የሚሆኑት ህጻናት የሞታቸው መንሳኤ የንፁህ ውሃ አቅርቦት ባለመኖሩ ከሚፈጠር የጤና ቀውስ ጋር የተያያዘ ነው።
ይህ በእንዲህ አንዳለ ዩኒሴፍ በአፍሪካ ውስጥ ያሉ ህጻናት በሞት አፋፍ ላይ እንደሆኑ እወቁልኝ ብሏል። የተባበሩት መንግስታት የህጻናት ፈንድ ዩኒሴፍ በአፍሪካ ቀንድ እና በሰፊው የሳህል ክልል ውስጥ ያሉ ህጻናት አስቸኳይ ድጋፍ ካልተደገላቸው በቀር ቁጥራቸው ይሄ ነው ያልተባሉ ህጻናት ለህልፈት ሊዳረጉ ይችላሉ ነው ያለው ።
ለንግግሬ ማሳያ ይሆንልኛል ብሎ እንደጠቀሰው መረጃ ባለፉት አምስት ወራት በኢትዮጵያ፣ በኬንያ እና በሶማሊያ አስተማማኝ የንፁህ ውሃ አቅርቦት የሌላቸው ሰዎች ቁጥር ከ9.5 ሚሊዮን ወደ 16.2 ሚሊዮን ከፍ ብሏል።
ይህ ቀውስ ለከፋ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት መስፋፋት እና ለውሃ ወለድ በሽታዎች ተጋላጭ ያደርጋል። በአፍሪካ ቀንድ አብዛኛው ሰው በጭነት መኪና ወይም በአህያ ጋሪ ላይ ሻጮች በሚያደርሱት ውሃ ላይ ጥገኛ ነው።
ከየትኛውም የአለም ክፍል በበለጠ ብዙ ህፃናት ህይወታቸውን ያጡበታል በሚባልለት ሳህል ቀጠና ዜጎች የሚያስፈልጋቸው የውሃ መጠንና ያለው ለየ ቅል ነው ተብሏል።
የአፍሪካ ዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል ፌዴሬሽን ቀጣናዊ ዳይሬክተር መሃመድ ኡመር ለሲጂቲኤን ሲናገሩ
“የዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ቀውስ ያስከተለውን ተፅዕኖ በተመለከተ ይህ በአፍሪካ ካጋጠመን ድርቅ እጅግ የከፋ ነው። ላለፉት 40 እና 50 ዓመታት ያህል እንዲህ አይነት ድርቅ አጋጥሞን አያውቅም።”
ኬንያን ስንመለከት ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት የውሃ ምንጮቿ እንደ ኩሬ እና ክፍት ጉድጓዶች ናቸው። በድርቅ በተጠቁ የኬኒያ አካባቢዎችም ጉድጓዶቹ የያዙት ውሃ ተሟጧል አልያም እንደደረቁ ነው የሚነገረው ። ይህም በሽታ ሊያስከስት ይችላል ተብሎ ተፈርቷል።
በሳሄል አካባቢ የውሃ አቅርቦትም ባለፉት 20 ዓመታት ከ40 በመቶ በላይ ቀንሷል። ይህ ከፍተኛ የውሃ ሃብት ማሽቆልቆል በአብዛኛው በአየር ንብረት ለውጥ እና በግጭቶች ሳቢያ ነው።
የዚህ የጸጥታ እጦት ውጤትም በቀጠናው ባለፉት ስድስት አመታት ተከስቶ የነበረውን አስከፊ የኮሌራ ወረርሽኝ አባብሶታል። በቀጠናው በወረርሽኙም 5,610 ዜጎች ሲጠቁ ፤170 ሰዎች መሞታቸው ተነግሯል።
በተለይም በሶማሊያ የኮሌራ ወረርሽኝ በድርቅ በተጠቁ ወረዳዎች በሙሉ ማለት ይቻላል ተከስቷል።
ቀድሞውንም 2.8 ሚሊዮን ህጻናት የተመጣጠነ የምግብ ችግር አለባቸው በተባለበት፤ የውሃ እጥረቱ ሲታከልበት ደግሞ በውሃ ወለድ በሽታ የመሞት እድላቸውን በ11 እጥፍ ይጨምረዋል ሲል ዩኒሴፍ አስታውቋል።
ከእነዚህ ተጎጂዎች ውስጥ ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት መሆናቸው ጉዳዩን የበለጠ አሳሳቢ አድርጎታል።
ባለፈው አንድ አመት ዩኒሴፍ እና አጋሮቹ በኢትዮጵያ ድርቅ በተከሰትባችው አካባቢዎች ከ5 አመት በታች የሆኑ 1.2 ሚሊዮን ዜጎችን አግዘዋል ይላል የዩኒሴፍ መረጃ ።
ዩኒሴፍ እንደሚለው በቀጥታ ለውሃ፣ ለአካባቢ ጽዳትና ለግል ንፅህና መጠበቂያ የሚሆን የገንዘብ ድጋፍ ለተጎጂዎች እየደረሰ አይደልም ብሏል።
በመቅደስ እንዳለ
2022-08-23