ሀገሬ ቲቪ

“አንድ ክራንች 30ሺህ ብር እየተሸጠ ነው” የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን

በሀገራችን ያሉ አካል ጉዳተኞች በዕለት ተዕለት የኑሮ ውጣ ውረድ ውስጥ ለተለያዩ ችግሮች እንደሚጋለጡ በተደጋጋሚ ይነገራል። የአካል ድጋፍ እጥረት ደግሞ እነዚህ ዜጎች ከሚቸገሩባቸው ጉዳዮች በዋናነት መጠቀስ የሚችል ነው።

የአካል ድጋፍ አካል ጉዳተኞች በእለታዊ ኑሮአቸው ለማከናውን የሚረዷቸው እንደ ክራንች፣ ዊልቸር፣ በትሮች፣ ሰውሰራሽ እግር እና እጅ ያሉ መሰል መሳሪያዎች ናቸው።

በኢትይዮጵያ እነዚህን የአካል ድጋፍ እንደልብ ማግኘት አለመቻሉ አካልጉዳተኛ ዜጎችን ዋጋ እያስከፈለ መኾኑን የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን ለጣቢያችን ተናግሯል።

አንድ ክራንች 30 ሺህ ብር እየተሸጠ በመኾኑ መግዛት እንኳን የማይቻልበት ደረጃ ላይ መደረሱን የማኅበሩ ፕሬዝዳንት አቶ አባይነህ ጎጆ ነግረውናል።

በዚህ ችግር ምክንያት አካል ጉዳተኞች በተለያዩ ማኀበራዊ ጉዳዮች ላይ ተሳታፊ የመኾን አቅም እና እድላቸውን እንደገደበው ነው አቶ ዓባይ ነህ የተናገሩት ለአብነትም በትምህርት መስኩ በርካታ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ተገደዋል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ያሉ አካል ጉዳተኞች እንደ ቀይ መስቀል ባሉ ረጂ ድርጅቶች አማካኝነት የሚለገሱ የአካል ድጋፎችን በማግኘት እየተገለገሉ እንደኾነው ነው የሰማነው።

በሀገሪቱ ሰፋ ያለ የአካል ድጋፍ የሚያመርት ተቋም ባለመኖሩ እነዚህ ለጋሽ ድርጅቶች ይኽን ድጋፋቸውን ቢያቋርጡ ከአሁኑ የባሰ ከባድ ችግር ላይ መውደቃችን የማይቀር ነው ሲሉ አቶ ዓባይ ነህ ተናግረዋል።

መንግሥት አሁን ላይ ይህን ችግር ተረድቶ ሰፋ ያለ የአካል ድጋፍ ማዕከል እንዲገነባ እያደረገ ነው ተብሏል። ይሕ ማዕከል የአካል ድጋፍ አቅርቦት እጥረቱን የሚፈታም ነው ተብሎለታል።

በኢትዮጵያ በአጠቃላይ ከ 20 ሚሊዮን በላይ አካል ጉዳተኞች እንዳሉ ይገመታል።

በሙሉጌታ በላይ
2022-08-24