ሀገሬ ቲቪ

ለኢትዮጵያ ብቁ ዲፕሎማት የሆኑት ዲያስፖራዎች

አብይ አህመድ (ዶ/ር) ዲያስፖራዎች ለኢትዮጵያ ብቁ ዲፕሎማት ናቸው አሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሀገር ልጅነታችሁን እንድታሳዩ ለቀረበላችሁ ጥሪ ምላሽ የሰጣችሁ እንኳን ደህና መጣችሁ ሲሉ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ዲያስፖራ ወገኖቻችን ለኢትዮጵያ ሲሉ በአንድነት ቆመዋል፣የፖለቲከኞችን በሮች አንኳኩተዋል፣አደባባዮችን በሰልፍ አጥለቅልቀዋል፣ ታላላቅ ተቋማትን ሞግተዋል፣ የመሪዎችን የተሳሳተ ፖሊሲ ተጋፍጠዋል፣ሚዲያዎች የኢትዮጵያን እውነት እንዲያንጸባርቁ ጫና ፈጥረዋል፡፡ የሕወሐት ቡድን በወገናችን ላይ ያደረሰውን ልክ የሌለው ግፍና መከራ በዓይናችሁ አይታችሁ ዓይኔን ግንባር ያርገው ላለው ዓለም እንዲገልጡ አሳስበዋል፡፡ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ሰፋ ያላ መግለጫ ያወጡት ዶ/ር አብይ ሀገር በአንድ ግዙፍ ቤተሰብ ሊመሰል ይችላል ብለዋል፡፡ አንድ ቤተሰብ የቆመበት መሠረት ጥንካሬ የሚታወቀው ከደስታ ጊዜያት ይልቅ ቤተሰቡ ችግር በገጠመው ወቅት ነው ፡፡ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች ሀገራችን ሰው በፈለገችበት ጊዜ ለሀገራቸው የቁርጥ ቀን ልጆች መሆናቸውን አስመስክረዋል ብለዋ፡፡ ሀገራቸው ‹ወደ እናት ሀገራቸሁ አንድ ሚልዮን ሆናችሁ ኑ!› ስትላቸውም፣ ጨርቄን ማቄን ሳይሉ ይሄው መጥተዋል፡፡ የእናት ቤት ከምንም ይበልጣል፤ በየመሥሪያ ቤቱ፣ በየንግድ ተቋማቱ በየአገልግሎት መስጫዎቹ የለመዳችሁትን ዓይነት ቀልጣፋና ዘመናዊ አሠራር ባታገኙ አይግረማችሁ። የእናታችሁ ቤት ነውና እንዴት እናዘምነው ብላችሁ አስቡበት እንጂ እንደ ባዳ አይታችሁ አትለፉት። አንዳንድ ተቋማት ባዘጋጇቸው መርሐ ግብሮችም ላይ ተሳተፉ፣ የቱሪስት መዳረሻዎችንም ጎብኙ፣የልማት ሥራዎቻችንንም ተመልከቱ በማለት ጥሪ አቅረበዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ከወላጆቻችሁ፣ ከዘመዶቻችሁና ከወዳጆቻችሁ ጋር መልካም ጊዜ አሳልፉ ሲሉ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡

በሀገሬ ቲቪ
2021-12-27