በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የፋይናንስ አካታችነት መጠን 45 በመቶ ብቻ ነው ተባለ። ይህ ማለት 30 ሚሊዮን ዜጋ ምንም ዓይነት ሂሳብ በፋይናንስ ተቋማት የለውም እንደ ማለት ነው ።
ይህም ቁጥር ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ ሀገራት ጋር ተነጻጽሮ ሲሰላ ሀገሪቱን እታችኛው ወለል ላይ ያስቀምጣታል ነው የተባለው ።
የፋይናንስ አካታችነት የሚለው ሲፍታታም በፋይናንስ ዘርፉ ሂሳብ የሌለው ወይም ያልተካተተውን ህብረተሰብ ማካተት እንደሆነ የዘርፉ ሙያተኞች ይናገራሉ ።
ይህ የተባለው የብሄራዊ ባንክ በ2014 የከወናቸውን ስራዎች በተመለከተ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ በሰጠበት ነው። ይህ የቁጥር መቀነስ ባንኮች የባለጸጎች ናቸው ከሚለው የህብረስብ ግንዛቤ ጋር የተያያዘ እንደሆነም ይነገራል።
የፋይናንስ ዘርፉ ዝቅተኛ ገቢ ያለውን ህብረተሰብ ታሳቢ ተደርገው ያልተቀረጹ መሆናቸው ሌላኛው ችግር ነው ሲሉ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ አካታችነት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተመስገን ዘለቀ ተናግረዋል።
ይህንንም ለመፍታት በሚል ብሄራዊ ባንክ ብሄራዊ የፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂ በሚኒስትሮች ምክር ቤት አጽድቋል። ባንኩ በሚቀጥሉት ዓመታት 70 በመቶ የሚሆነውን ጎልማሳ በፋይናንስ አካትታለሁ ብሏል።
የአዳዲስ ባንኮች ዘርፉን መቀላልቀል ከባንክ ውጪ ያለው ገንዘብ ወደ ባንክ እንዲገባ ስቦታል ተብሏል። የቴሌ ብር አገልግሎች መጀመር በያዝነው ዓመት 22 ሚሊዮን የዲጂታል ሂሳብ እንዲከፈት ሆኗል።
የዲጂታል ሂሳቦች ቁጥር በሞባይል 43.8 ሚሊዮን ፣ ሞባይል ባንኪንግ 16.3 ሚሊዮን ፣ የኢንተርኔት ባንኪንግ 4.4 ና በካርድ ባንኪንግ 30.8 ሚሊዮን ገንዘብ መዘዋወሩን የብሄራዊ ባንክ መረጃ ያሳያል።
በበጀት ዓመቱ የብድርና ቁጠባ ሂሳብ ሲቀንስ የኢንተርኔት ባንኪንግ ማየሉም ተገልጿል ።
በመቅደስ እንዳለ
2022-08-24
