ሀገሬ ቲቪ

ዩክሬይን ከሶቭየት ህብረት ነጻ የወጣችባት ዕለት

የምስራቅ አውሮፓዊቷ ሀገር ዩክሬይን ዛሬ ላይ የምዕራባውያኑ እና የሩስያ የፍጥጫ ስፍራ ሆናለች። የኔቶን ወደ ምስራቅ አውሮፓ መስፋፋት አልወደድኩትም ያለችው ሩስያ ጋር ጦርነት ከገባች መንፈቅ አመት ሞላት።

ይህችው ሀገር ዩክሬይን ከሶቭየት ህብረት ነጻ የወጣችው በዛሬዋ ዕለት ከ30 ዓመታት በፊት ነበር። የዩክሬይን የሀገርነት ስሜት መነሳሳት የጀመረው በ18ኛው ክፍለ ዘመን ማብቂያ እና በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ ነበር።

በሩስያ ቦልሸቪክ ስልጣን ከያዘ በኋላ ከሴንትራል ፓወር ኃይሎች ጋር ሰላም ለማውረድ በተደረገው ድርድር የቀድሞ የሩስያ ግዛት አካል የነበረችው ዩክሬይን ሙሉ ነጻነቷን በ1910 ዓ.ም. አውጃ ነበር።ዳግም በሶቭየት ህብረት ብትጠቀለልም።

የሩስያ አካል የነበረችው ዩክሬይን ሰፊ እና ባለጸጋዋ ስፍራ ነበረች። ዩክሬይን በአውሮፓ ትልቅ ስንዴ አምራች፣ የብረት እና ከሰል ምርቶችን ጨምሮ የማዕድን ሀብቶችም ምንጭ የነበረች ናት።

የሶቭየት ህብረት ፕሬዝዳንት የነበሩትን ሚካኤል ጎርባቾቭን ከስልጣን ለማውረድ ከተደረገው ካልተሳካው መፈንቅለ መንግስት በኋላ የሀገሪቱ ምክር ቤት ከ30 ዓመታት በፊት በ1983 ዓ.ም. የዩክሬይንን ነጻነት አጽድቋል። በዚህም የዛሬዋ ዕለት የዩክሬይን የነጻነት ቀን ተደርጋ ትታሰባለች።

አብዛኛው የዩክሬይን ግዛት በጊዜው በነበረው የአውሮፓ ሁኔታ በ1780ዎቹ ፖላንድ ከተከፋፈለች በኋላ ወደ ሩስያ መንግስት የገባ ነው። ቀሪው ክፍል ደግሞ በአውስትሮ-ሃንጋሪ ስር የነበረ ሲሆን በአንደኛው የዓለም ጦርነት የምስራቅ ግንባር የጦርነት ስፍራ ነበር።

በሩስያ አብዮት ሩስያን ለ350 ዓመታት ካስተዳደረው የሲዛር መንግስት መውደቅ በኋላ በ1909 ዓ.ም. ዩክሬይን ጊዜያዊ መንግስት አቋቁማ በፌደራላዊ ሩስያ ስር የራሷን ሪፐብሊክ አወጀች።

ቭላድሚር ሌኒን እና ፓርቲያቸው ቦልሸቪክ ወደስልጣን ከመጡ በኋላ ዩክሬይን እንደቀድሞዋ ሩስያ ክፍል ፊንላንድ ሁሉ በ1910 ዓ.ም. ሙሉ ነጻ ነኝ ስትል አወጀች።

የሀገሪቱ መንግስት ራዳ ግን ከሶቭየት ከመለያየቱ በኋላ የሶቭየት ቦልሸቪክ ተቃውሞን እና የሀገር ውስጥ የጸረ አብዮት እንቅስቃሴዎችን ተቋቁሞ ሙሉ ለሙሉ ሀገሪቱን ለማስተዳደር አልተቻለውም።

በረሃብ ለተጠቁ ህዝቦቻቸው የምግብ ምንጭ አድርገው ዩክሬይንን ያሰቧት ኦስትርያ እና ጀርመን ስርዓት ለማስጠበቅ በሚል ወታደሮቻቸውን አስገቡ።

የሶቭየት ወታደሮችን እንዲወጡም መጋቢት ላይ በ1910 ዓ.ም. ባደረጉት ስምምነት አስገደዷቸው። የዩክሬይንን ነጻነት እናከብራለን ቢሉን በሚታይ መንገድ ዩክሬይንን ያዟት።

የሴንትራል ፓወር ኃይሎች በመሸነፋቸው ጀርመን እና ኦስትርያ ዩክሬይንን ለቀው እንዲወጡ ምክንያት ሆኗል። በተመሳሳይም የኦስትሮሃንጋሪ መውደቅ የዩክሬይን ግዛቶች በ1911 ዓ.ም. እንዲዋሃዱ ምክኛት ሆኗል።

ግን ደግሞ የነጻነት ጊዜያቸው ለአጭር ጊዜ ብቻ የቆየ ነበር። ከፖላንድ እና ሩስያ ጋር መዋጋት ጀመሩ። ዩክሬይን ለአጭር ጊዜ ከፖላንድ ጋር ብትተባበርም የሶቭየት ጥቃትን ግን መቋቋም አልተቻላትም።

በ1916 ዓ.ም. የሶቭየት ህብረትን ጥቃት መቋቋም ያልቻለችው ዩክሬይን ከሶቭየት የሶሽያሊስት ሪፐብሊክ ህብረት አንዷ ሆነች። ሶቭየት ህብረት በ1983 ዓ.ም. በይፋ እስክትበተንም ነጻነቷን አላገኘችም።

ከሶቭየት ህብረት መውደቅ በኋላ ግን ምክር ቤቱ ከ30 ዓመታት በፊት የዩክሬይንን ነጻነት ካጸደቀ በኋላ ነጻ ሆናለች። ከዚያ ወዲህም ቢሆን ግን ከሩስያ ጋር ሰላም አልሆነችም።

በ2006 ዓ.ም. ባደረጉት ጦርነት ክሪሚያን ከዩክሬይን የነጠቀችው ሩስያ ዛሬ ላይ ደግሞ የኔቶ ወደ ምስራቅ አውሮፓ መስፋፋት አልጣመኝም በሚል ዩክሬይን የጦርነት አውደማ ካረገቻት መንፈቅ ሆኗታል። የነጻነት ቀኗን በደማቅ ለማክበርም ቢሆን የሩስያ ጥቃት ስጋት እክል ሆኗታል።

ምዕራባውያኑም ቢሆኑ በዳር አይዞሽ እያሏት በአለንሽ ከዚህ ቢያደርሷትም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በአውሮፓ ትልቁ የተባለለትን የሩስያን ዘመቻ በመንፈቅ የጦር አውድማነት እያስተናገደችው ነው። የነጻነት ቀኗን በጦፈ ጦርነት ውስጥ ሆና ማሰቡም የግድ ሆኖባታል።

በአብርሃም በለጠ
2022-08-24