ሀገሬ ቲቪ

የጭነት መኪናውን ወደ ልዕልት መኝታ ቤትነት የቀየረው አባት

አባትነት! የተፈጥሮ ድንቅ ስጦታ ነው። አባቶች ለልጆቻቸው ያላቸውን ፍቅር ያላቸውን ሳይሰስቱ በመስጠት ይገልፁታል። አሁን የምነግራችሁም ታሪክ የዚህ መገለጫ ነው።

ሰዎቹ የደቡብ ምእራብ ቻይና ዩናን ግዛት ነዋሪ ናቸው። ከወደቻይና የሚኖሩ ባለትዳሮች አንድ ነገር ያስጨንቃቸዋል፤ አልገፋ የሚለውን ኑሮ ለማሸነፍ ደፋ ቀና ማለታቸው ለልጃቸው ግዜ እንዳይሰጡ አድርጓቸዋል እና።

በስራ ተወጥረው ቀኑን የሚሻገሩት አባወራውና እማወራዋ ቀደም ሲል ልጃቸውን አያታቸው ዘንድ ትተዋት ነበር በጭነት መኲናቸው ላይ የሚያሳልፉት።

አሁን ግን ነገሮች የተለወጡ ይመስላሉ፤ አባት የጭነት መኪናውን ውስጠኛ ክፍል የልዕልት መኝታ ቤት እስኪመስል ድረስ አስውቦታል።

በ20 ዓመታቸው የጭነት መኪና ወደ ማሽከርከር እንደገቡ የምትናገረዋ እናት በዚህም ሳቢያ ለልጃቸው ግዜን ለመስጠት ተቸግረው እንደነበር ትናገራለች።

አራት ዓመት የሞላት ልጃቸው አሁን በመኪናው ውስጥ ተመችቷት እንዳሻት ትሆናለች። መኪናው ከዳሽ ቦርዱ እስከ ማረፊያው ድረስ በምቹ የልጆች ምንጣፍ እና በአሻንጉሊቶች ያሸበረቀ ነው።

ከእኛ ጋር በመንገዱ ላይ መመላለስ ያስደስታታል የምትለው እናት ባሏ የዘየደው መላ ከልጃቸው ጋር ግዜ ለማሳለፍ ግዜ ከማግኘት ባለፈ ልጃቸውን ደስተኛ እንዳደረገላት ተናግራለች።

በቻይኖቹ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴ ላይ የመኪናው ውስጣዊ ሁኔታ ከታየ በኋላ ግርምትን አጭሯል። እንዴት አይነት አባት ነው ሲሉ ያቆለጳጰሱም አልታጡም።

ቪዲዮውም 110 ሚሊዮን ያህል ተመልካቾችን በማግኘት ዝነኛ ሆኗል። መልካም አባትነት ይህ አይደል።

በሳምሶን ገድሉ
2022-08-24