ሀገሬ ቲቪ

ሽርክና የፈጠረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዛምቢያ ያቋቋመው አዲስ አየር መንገድ የፊታችን ዕሮብ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል፡፡ አየር መንገዱ የዛምቢያ መንግሥት ንብረት ከሆነው ኢንደስትሪያል ዴቨሎፕመንት ኮርፖሬሽን ከተሰኘ ድርጅት ጋር በሽርክና ዛምቢያ ኤርዌይስ የተሰኘ አዲስ አየር መንገድ በማቋቋም ላይ ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዛምቢያ ኤርዌይስ ላይ የ45 በመቶ ድርሻ ያለው ሲሆን ኢንደስትሪያል ዴቨሎፕመንት ኮርፖሬሽን ደግሞ 55 በመቶ ድርሻ እንዳለው ተገልጿል፡፡ ሁለቱ ባለአክሲዮኖች 30 ሚሊዮን ዶላር ለአየር መንገዱ መመስረቻ ካፒታል ማውጣታቸውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ መግለጫ ያመላክታል፡፡ አዲሱ አየር መንገድ ዕሮብ ህዳር 22 በሀገር ውስጥ በረራ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በቀጣይ ክልላዊ የበረራ አገልግሎት ወደ ጆሀንስበርግ ደቡብ አፍሪካ እና ሀራሬ ዚምባብዌ በመጪው የፈረንጆቹ ዓመት እንደሚጀምርም ተገልጿል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተወልደ ገ/ማርያም የዛምቢያ ኤርዌይስ መመስረት በኢትዮጵያ አየርመንገድ በራዕይ 2025 የእድገት ስትራቴጂ የተለያዩ ክልላዊ መናህሪያዎችን ለማቋቋም የተቀመጠው ግብ አካል ነው ብለዋል፡፡ ዛምቢያ ኤርዌይስ በመካከለኛው እና ደቡብ አፍሪካ ጠንካራ መናህሪያ እንደሚሆን ያላቸውን እምነትም ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቶጎ፣ ማላዊ፣ ቻድ እና ሞዛምቢክ አየር መንገዶችን በሽርክና ማቋቋሙ ይታወሳል፡፡

በሀገሬ ቴቪ
2021-06-04