ሀገሬ ቲቪ

በፋሽስት ወረራ ጊዜ የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ፌደሬሽን ምስረታ

ታሪክን መለስ ብለው ሲቃኙት ኢትዮጵያ የሚለው ስም ገናና ሆኖ መገኘቱ አይቀሬ ሃቅ ነው። ለመላው ዓለም ጥቁር ፣ ለአፍሪካውያን የኩራት ምንጭ የሆነ ስምም ነው።

ከአድዋ ድል አርባ ዓመታት በኋላ ቂም ቋጥሮ የመጣው ጣሊያን ኢትዮጵያን ሲወጋ በአሜሪካ ያሉ ጥቁሮች በልባቸው ለመነኑላት ኢትዮጵያ ካልዘመትን አሉ። ይህን ካሉበት አንዱ የነበረው የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ፌደሬሽን በዛሬዋ ዕለት በ1929 ዓ.ም. ነበር የተቋቋመው። የዕለቱን ከታሪክ ትኩረታችን ነው።

አፍሪካን የመቀራመት የአውሮፓውያን ክፉ ምኞት በአድዋ ተራሮች ኢትዮጵያውያን በደማቸው ማብቂያ ያለው ሁነት መሆኑን ለዓለም ሹክ ብለዋል። ይህ ሁነት ደግሞ ኢትዮጵያ የሚለውን ስም በዓለም ጥቁሮች እና ግፉዓን ልብ ውስጥ በክብር እንዲቀመጥ አድርጓል።

ባሉን የጦር መሳሪያዎች፣ በገዛናቸውም ጭምር የዘመነውን ጦር በአንድነት በልጠነው ድል ከነሳን 40 ዓመታት ካለፉ በኋላ ፋሽስት ጣሊያን ከነቂሙ ከዘመናዊ ጦሩ ጋር ወደ ምስራቅ አፍሪካዋ የጥቁሮች ኩራት ኢትዮጵያ ለወረራ መጣ።

ብዙም የዘመኑን የጦር መሳሪያ በእጃችን ሳናካብት ከአራት አስርት ዓመታት በኋላ የመጣው የፋሽስት ኢትዮጵያን መውረር ግን ኢትዮጵያን ለሚወዱ ጥቁሮች የሚቀበሉት አልሆነላቸውም።

ይሄንን የጣሊያን ሁለተኛ ወረራን ለመመከት እና ኢትዮጵያን ከወረራው ለመታደግ በሚል ኢትዮጵያን የሚወዱ ጥቁሮችን ያቀፈው የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ፌደሬሽን ከ85 አመታት በፊት በዛሬዋ ዕለት በአሜሪካ ተቋቋመ።

የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ፌደሬሽን(Ethiopian World Federation) የመቋቋሙ ምክንያት ጣሊያን ዳግም ኢትዮጵያን የመውረሩ ቁጭት ነበር። ጥቁሮች በአሜሪካ ምድር የነጻነት ምልክታቸው የሆነችው ኢትዮጵያን ስለሚታደጉበት መንገድ መማከር ጀምረዋል። በጊዜው በአሜሪካ የነበሩት መላኩ ኢማኑኤል በያን (ዶ/ር) ለፌደሬሽኑ መመስረት ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።

መላኩ በያን ከአሜሪካ ኮሌጅ የተመረቁ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ሰው ናቸው። የህክምና ሙያ ባለቤት የነበሩት መላኩ በያን የፓን አፍሪካን እሳቤ የነበራቸው ሲሆን በጥቁሮች ህብረት የሚያምኑ ነበሩ። ከጥቁሮች እና ኢትዮጵያውያን ጋርም በአሜሪካ የቅርብ ግንኙነት እንዲኖር የሚያደርጉ ሰው ነበሩ።

የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ፌደሬሽኑ እንዲመሰረትም ዶ/ር መላኩ በያን ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል። ፌደሬሽኑ በኒው ዮርክ አሜሪካ ከመመስረቱ በተጨማሪ በካሪቢያን እና በአውሮፓ ቅርንጫፎች የነበረው ነበር። በተለይም በካሪቢያን የራስ ተፈሪያን እንቅስቃሴ ለመጀመሩም የራሱን አስተዋጽኦ አበርክቷል።

ለኢትዮጵያ የጣሊያን ወረራን ለመከላከልም የገንዘብ ድጋፍ የማድረግ እንቅስቃሴዎች አድርጓል። በርግጥ የተለያዩ ችግሮች ድጋፉን ለማድረስ ችግሮች ቢገጥሙትም ጠንከር ብሎ የተደራጀ የጣሊያንን ወረራ ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም የተቃወመ ቡድን ሆኗል።

ዶ/ር መላኩ በያን ወደ ሃገሩ በመመለስ በጣሊያን ወረራ መጀመሪያ በኦጋዴን ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ጋር የህክምና አገልግሎት ሰጥተዋል። ኋላም የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የግል ሃኪም በመሆን አገልግለዋል። የግል ሃኪማቸው ከመሆናቸው በተጨማሪ አማካሪም ጭምር የነበሩት ዶ/ር መላኩ ወደ ጀኔቫ ከንጉሱ ጋርም ሄደዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጂት ኢትዮጵያን ከጣሊያን ወረራ ለመታደግ ዝግጁ አለመሆኑን በመታዘብም ወደ አሜሪካ በመሄድ የኢትዮጵያ ተወካይ እና ድጋፍ አሰባሳቢ ሆነዋል። ከነጮች ይልቅ የጥቁሮችን የህብረት መተጋገዝ ላይ ተስፋቸውን ጥለዋል።

መላኩ በያን ከጥቁሮች ጋር ያለውን ህብረት ለማጠንከር በጊዜው ከነበሩ የጥቁሮች ማህበራት ጋር ከመስራታቸውም በተጨማሪ ሀገራቸው ላይ የተከፈተውን ወረራ ለመቀልበስ የሚያስችል ኢትዮጵያን የሚደግፍ ማህበር ለመስረት ከጥቁሮች ጋር ጥሩ ግንኙነት እና ተቀባይነትን መፍጠር ችለዋል።

ይህን እያደረጉ ባሉበትም ቢሆን ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጋር ግንኙነት ማድረጋቸው አልቀረም። የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ፌደሬሽን መመስረቱም ከዚሁ ጋር በተያያዘ ነው። ለኢትዮጵያ በፌደሬሽኑ በኩል ሃብታቸውን ከመስጠታቸው ባሻገር ህይወታቸውን ለመስጠት የተዘጋጁ ጥቁሮችም አልታጡም ነበር።

መላኩ በያንም የኢትዮጵያን ከጣሊያን ነጻ መውጣት ለማየት አንድ ዓመት ሲቀራቸው በ40 ዓመታቸው ህይወታቸው እስኪያልፍ ለኢትዮጵያ ሰርተዋል።

ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከነጻነት በኋላ በ1940 ዓ.ም. ደግሞ ለጥቁሮች የ500 ሄክታር መሬትን በሻሽመኔ ሰጥተዋል።

በአብርሃም በለጠ
2022-08-25