ሀገሬ ቲቪ

አንድ ቻይናዊ መንደሩን እያስዋበ ነው

የአካባቢ ውበት የሁሉም ጉዳይ ነው ፤ ትኩረት ያስፈልገዋል ሲባል በተደጋጋሚ እንሰማለን። ብዙዎቻችን ቤታችን ከማስዋብ አልፈን አካባቢያችንን ውበት የማጎናጸፍ ልምድ እምብዛም የለንም ።

የአካባቢን ጽዳት ጠብቆና እስውቦ ከራስ እርካት ባለፈ ለከተማ የገቢ ምንጭ ማድረግን አንድ ቻይናዊ ከውኖታል መባሉን ሰማን።በደቡብ ምዕራብ ቻይና ዩናን ግዛት ነዋሪ የሆነው ይህ ወጣት በቀለም ብሩሽ መንደሩ አዲስ ገጽታ ለማላበስ ነው የሰራው ።

አሁን አሁን በኢንሰተግራም የተወደዱ ምስሎችን በግድግዳ ላይ የሚከትበው የስዕል ጠበብቱ ሊዩ ዢያኦቤይ የትውልድ ቀዬውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ እያሳደገ መሆኑንም ሲጂቲኤን ዘግቧል።

የሀገሬው ነዋሪዎች እዚህ ግባ የማይባል የቤት ግድግዳ እንኳን ቢሆን የእርሱ እጆች ሲያርፉባቸው ሕይወት ይዘራባቸዋል እያሉ ያሞካሹታል።

የሃያ ሰባት ዓመቱ ሰዓሊ ከዚህ ቀደም እንደ ቾንግኪንግ ባሉ ትልልቅ ከተሞች ውስጥ ይስል ነበር ተብሏል። በከተማው የሰራው ምስልም ዝነኛ አድርጎታል ።

ባለፈው ዓመት በደቡብ ምዕራብ ዩናን ግዛት ወደምትገኘው ቄየው ለመመለስ እንደወሰነም ይናገራል። የግድግዳው ሰዓሊ ሊዩ ዢያኦቤይ ለሲጂቲኤን ይህንን ብሏል።

“የእኔ ሥዕሎች በትውልድ መንደሬ ብዙ ቱሪዝም ቢያፈሩና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን እንዲያመጡ እመኛለሁ። ይህ የመጨረሻ ግቤ ነው።”

መጀመሪያ ላይ ብዙ የመንደሩ ነዋሪዎች ምንም እንኳን ከክፍያ ነጻ ስራ እየሰራ ቢሆንም የፈጠራ ሀሳቡን አልተረዱም ነበር።በአንደኛው የፈጠራ ስዕሉ መጥፎ ዕድል እንደሚያመጣ ያመኑ እድሜያቸው ገፋ ያሉ አንዲት ሴት ስዕሉን ሊያጠፉት እንደቻሉ ሰዓሊው ይናገራል።

“በሰዓቱ የተደበላለቁ ስሜቶች ነበር የተሰሙኝ ፤ትንሽ ተናድጄም ነበር ፤አዝኛለሁም። በመጨረሻም እሳቸውን ለመረዳት ሞከርኩኝ ። በጥቃቅን ጉዳዮች ከጎረቤቶቼ ጋር ግብግብ መፍጠር አልፈልግም ይልቁንም ከጎረቤቶቼ ጋር እንዴት መግባባት እንዳለብኝ ነው የተማርኩት”

አሁን መንደሩ በተለያዩ የሰዓሊው ስራዎች የተንቆጠቆጠ ሆኗል። ስዕሉ አንድ ሳምንት ገደማ ጊዜን ፈጅቷል ፤ የመንደሩ ነዋሪዎችም ግድግዳቸውን እንዲቀባላቸው ግብዣ አቅርበውለታል።

ብዙዎች ፎቶ ለማንሳት ወደስፍራው እየተመሙ ነው ፤ የቻይና ባህልን በማጉላት የበለጠ ለመሳል አቅዷል። ሥዕሎቹ በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ላይ ከተለጠፉ በኋላ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሆኗል። አሁን ላይ በተለያዩ የማኅበራዊ ገጾች ከአንድ ሚሊዮን በላይ ተከታዮች አሉት።

በመቅደስ እንዳለ
2022-08-25