ሀገሬ ቲቪ

የተፈጥሮ አየር በብልቃጥ የሚሸጠው ወጣት

እንኖርባት ዘንድ የተሰጠችን ዓለም አሁን ወደማብቂያዋ ተጠግታለች፤ የተመራማሪዎች ሀሳብ ነው። ምክንያቱ ደግሞ እራሱ የሰው ልጅ ነው። ምድርን ለሰዎች መኖሪያ የተሻለ አድርጎ ሊያበጃት ሲገባው፤ በገዛ እጁ መጨረሻዋን እያፋጠነ ነው።

የአየር ንብረት መለወጥ የሰዎችን እድሜ በእጅጉ እየቀነሰው ስለመሆኑ ከዚህ ቀደም ነግረናችሁ ነበር። ይሄው የአየር ንብረት ለውጥ ሰዎች የሚንተነፍሰውን አየር የተበከለ እንደሚያድደርገው ተመራማሪዎቹ ደጋግመው ነግረውናል።

ታዲያ ከወደ ኮሎምቢያ ያለ አንድ ወጣት ሙሉ በሙሉ ተፈጥሯዊ የሆነ አየርን በመሸጥ ኑሮውን ይገፋል መባሉን ሰማን እና ልናጋራችሁ ወደድን።

ደሞ ይሄ ምን ይሉት ንግድ ነው ሊያሰኛችሁ ይችላል። ነገሩ ግን እውነት ነው፤ ወጣቱ ሁዋን ካርሎስ አልቫራዶ የትውልድ ከተማውን አየር በጠርሙስ እየሞላ መሸጥ ከጀመረ ሰንበትበት ብሏል።

እንደ ኦዲቲ ሴንትራል ዘገባ ከሆነ በኮሎምቢያ ካሉ ከተሞች ሁለተኛዋ ትልቋ ከተማ ሜዴሊን ብክለትን በማያውቀው በመልካም አየሯ ስማቸው ከሚነሱ ከተሞች መካከል ቀዳሚዋ ናት። ለዘላለሙ ጸደይ የሆነች ከተማም ይሏታል፤ ይላል ዘገባው።

አየርን በጠርሙስ ሞልቶ መሸጥን እንዴት አሰበው የበርካቶቻችን ጥያቄ ነው።

መቼስ የአየር ንብረት ነገር ሰላም ያልነሳው ሀገር ማግኘት ከባድ ነው፤ ታዲያ አየራቸው ለሰው ተፈጥሮ ለተቸገሩ ሀገራት ሰዎች የተጣራ ንጹ የተፈጥሮ አየርን ይሸጣሉ የሚለው ወሬ ከጆሮው መድረሱ መነሳሳትን እንዳሳደረበት ዘገባው አትቷል።

ካለማንም ከልካይ እንዳሻን የምንምገው አየር አሁን ውድ እየሆነ የመጣ ይመስላል። አሁን ባለው ሁኔታ ይላል አልቫራዶ አሁን ባለው ሁኔታ የከተማችንን አየር እናጠራቅማለን ከዚያም በንፁህ እና ሌላ ተጨማሪ ሽታ በሌላቸው ትናንሽ ብልቃጦች ውስጥ እናሽግ እና ለገበያ እናቀርባቸዋለን።

ታዲያ በትናንሽ ብልቃጦች ውስጥ የምንሸጠው የእኛ ከተማ አየር ጥራት ያለው መሆኑን አረጋግጣለው ሲልም በመተማመን መንፈስ ይናገራል።

የጠራውን አየርም ለመሰብሰብ የሚረዳ የተለየ መሳሪያን እንደፈተረ የሚናገረው ወጣቱ መቶ በመቶ የተጣራውን የተፈጥሮ አየር ለመሰብሰብ እና በብልቃጥ ውስጥ ለመሙላት ከ15 እስከ 30 ደቂቃዎችን እንደሚወስድ ተናግሯል።

ወጣቱ በመጀመሪያ ቀን ገበያው 77 ጠርሙሶችን በመሸጥ ገድ ማለቱን ይናገራል። ለእያንዳንዱ ጠርሙስም 5 ዶላርን ዋጋን ተምኖላቸዋል።

የመጀመሪያ ቀን ገድ ያለው የዚህ አየር ገበያ አሁን በቀን እስከ 300 ጠርሙሶችን ለቱሪስቶች ወደ መሸጥ አድርሶታል። ይህ የአልቫራዶ ፈጠራ በማህበራዊ ዘዴ ላይ የበርካቶች መነጋገሪያ ሆኗል።

የሀገሬው የብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያም ቢሆን ትኩረቱ በወጣቱ ፈጠራ ላይ ከሆነ ዋል አደር ብሏል። በዚህም ሳቢያ የወጣቱ ገበያ ደርቶለታል ነው የተባለው።

አንዳንዶች ታዲያ ባዶ ጠርሙስን አሽጎ መሸጥ ምን ይሉት ንግድ ነው ሲሉ ተደምጠዋል። አልቫራዶ ግን በዚህ አይስማማም እነዚያን ብልቃጦች በአየር መሙላት ቀላል የሚባል ጥበብን አይጠይቅም ብይ ነው።

ብቻ ምን አለፋችሁ ምድርን ተንከባክበን መያዝ ሲገባን እንደቀልድ ቸል ያልናቸው ቅንጣቶች አሁን ዋጋን እያስከፈሉን ይገኛሉ።

በሳምሶን ገድሉ
2022-08-26