ሀገሬ ቲቪ

ውጤታማ የፖልዮ ክትባት ያገኘው አልበርት ሳቢን

ፖልዮ ከፊል እና ሙሉ የሰውነት አለመታዘዝ ሊያስከትል የሚችል ህመም ነው። ይሄው በሽታ ምልክት የማያሳይ መሆኑ ደግሞ ስር ሳይሰድ ህክምና ማግኘትን ከባድ ያደርገዋል። በምርምሩ ዘርፍ ለፖሊዮ ክትባት በማግኘት በኩል አሻራቸውን ያሳረፉ ሰዎች አሉ።

ከነዚህ አንዱ የሆነው እና ፖልዮን በመከላከል እና በማጥፋት በኩል የተዋጣለት የፖልዮ ክትባትን ለዓለም ያበረከተው ዶ/ር አልበርት ሳቢን የተወለደው በዛሬዋ ዕለት በ1888 ዓ.ም. ነበር። የዕለቱን ከታሪክ ትኩረት ነው።

ፖልዮ በፖልዮ ቫይረስ የሚከሰት የነርቭ ጉዳትን በማምጣት የሰውነትን አለመታዘዝን ብሎም ለመተንፈስ መቸገርን በማስከተል እስከሞት የሚያደርስ በሽታ ነው።

ይሄው በሽታ በመላው ዓለም ስጋት የነበረ ሲሆን ዛሬ ላይ በክትባት ዘመቻዎች ሳቢያ ሁለት ሀገራት አፍጋኒስታን እና ፓኪስታን ላይ ብቻ ይገኛል።

ወደ 20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ መለስ ስንል ግን ይሄው የቫይረስ በሽታ ለዓለም ስጋት ነበር። በዚህ ጊዜ ታዲያ የመጀመሪያው ባይሆንም ውጤታማ መሆን የቻለውን የፖልዮ ክትባት ሩስያዊ እና አሜሪካዊ የሆነው የቫይረሶች አጥኝ አልበርት ሳቢን አግኝቷል።

ይሄንን ግኝቱን ለዓለም እንካችሁ ያለው ሰው ከ126 ዓመታት በፊት በዛሬዋ ዕለት በ1888 ዓ.ም. ነበር የተወለደው።የአልበርት ሳቢን በአፍ የሚሰጥ ክትባት በደቡብ አሜሪካ ጭንቅ የነበረውን ፖልዮን በማጥፋት በኩል የሚታይ ውጤት አስገኝቷል።

ምንም እንኳን የፖልዮ ክትባትን በማዘጋጀት በኩል ልጆችን ከመታደጉ ዓላማ በተጨማሪ በተመራማሪዎች መካከል ፉክክር የነበረ ቢሆንም የሳቢን ክትባት በምዕራቡ ዓለም ፖሊዮን በመከላከል በኩል የተዋጣለት ዘዴ ሆኖ ተገኝቷል።

በደቡብ አሜሪካም በሽታውን ለማጥፋት ‘’ሳቢን እሁድ’’ በዓመት ሁለት ጊዜ ይከበር ነበር። ምንም እንኳን ውጤታማ ክትባቱን ማግኘቱ ወደ ሀብት መቀየር የሚችል የነበረ ቢሆንም ያወጣቸውን ጥብቅ መስፈርቶች የሚያሟሉ ድርጂቶች በነጻ እንዲጠቀሙበት ፈቅዷል።

በሙሉ ስሙ አልበርት ብሩስ ሳቢን ተብሎ የሚጠራው ሳቢን የተወለደው ቀድሞ በሩስያ በሚገኝ አሁን በፖላንድ ባለ ስፍራ በብያሊስቶክ ነበር።

በ1910ዎቹ መጀመሪያም ከቤተሰቡ ጋር ወደ አሜሪካ ተጉዟል። በፔተርሰን ሲኖሩም በአክስቱ የገንዘብ ድጋፍ የጥርስ ህክምና መከታተል ቢጀምርም በቫይረስ ጥናት ዘርፍ በመሳቡ የጀመረውን ትምህርት አቋርጦ የቫይረስ ጥናት ትምህርቱን ለመከታተል የተለያዩ ስራዎችን በመስራት ራሱን ደግፏል።

በኒውዮርክ ዩኒቨርሲቲ ሲማርም የቤተ ሙከራ ቴክኒሻን በመሆንም ራሱን አግዟል። የመጀመሪያ ዲግሪውን ሲያገኝም የኒሞኒያ ቫይረስን መለየት የሚያስችል ጥናት አድርጓል።

የሁለተኛ ዲግሪውን በህክምናው ዘርፍ ካገኘም በኋላ ወደ እንግሊዝ በመሄድ ትምህርቱን ተከታትሏል። በዚያም የበሽታዎች ጥናት ላይ ከፍተኛ ምርምር አድርጓል።

አልበርት ሳቢን በሰዎች የነርቭ ህዋስ ውስጥ የፖልዮ ቫይረስ እድገት እንደሚኖርም በማሳየት የመጀመሪያው ተመራማሪ ነው። በኦሃዮ ሙሉ ፕሮፌሰር የሆነው ሳቢን ፖልዮ ላይ የሚያደርገውን ጥናት ቀጥሏል።

በ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ስጋት የሆነውን ፖልዮን መከላከል የሚያስችል ምርምር በማድረጉ በኩል ትልቅ አስተዋጽኦ ከነበራቸው ሰዎችም አንዱ ሆኗል። በ1940ዎቹ ሳቢን ባለበት አሜሪካ ብቻ 33 ሺህ ሰዎች በፖልዮ ተጠቅተዋል። ብዙዎቹ ደግሞ ልጆች ነበሩ። ማህበረሰቡንም አሸብሮ ነበር።

ደቡብ አሜሪካ ምዕራብ አውሮፓ ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ገብተዋል።አልበርት ሳቢን ደግሞ በጊዜው አስጨናቂ በነበረው የፖልዮ ወረርሽኝ ላይ ምርምር ማድረጉን ቀጥሎ የፖልዮ ክትባትን የማዘጋጀት ስራው ላይ አተኩሯል።

በዚህም ከሌላኛው በጊዜው የፖልዮ ክትባትን በማዘጋጀት በኩል ስሙ ከሚጠራው ጆናስ ሳልክ ጋር በየራሳቸው መንገድ ፉክክር ላይ ናቸው። በ1940ዎቹ ሳልክ ቀድሞ ክትባቱን በማግኘት ቢቀድምም 5 ልጆች የሱን ክትባት ከወሰዱ በኋላ በካሊፎርንያ በፖልዮ ተይዘው ተገኙ።

በአፍ የሚሰጥ የፖልዮ ክትባቱን ያገኘው ሳቢን ከሩስያኖች ጋር ስራውን ለማዳበር አብሮ ሰርቷል። ውጤታማ መሆኑም ተረጋግጦለታል። በሶቭየት ህብረት፣ በሜክሲኮ፣ በምስራቅ አውሮፓ፣ በሲንጋፖር እና በኔዘርላንድም በ100 ሚሊዮን ሰዎች ላይ ተሞክሮለታል።

በአሜሪካም ለሶስት አስርት ዓመታት የሳቢን ክትባት ፖልዮን በመከላከል እና በማጥፋት በኩል ተመራጭ ሆኖ መቆየት ችሏል። ሳቢን ለሌሎችም በሽታዎች ቢሆን ክትባትን አግኝቷል።

በህክምናው ዘርፍ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከት የቻለው ሳቢን የተለያዩ ሽልማቶቹን ስለስራዎቹ ማግኘት የቻለ ሲሆን በ1985 ዓ.ም. አርፏል።

በአብርሃም በለጠ
2022-08-26