
ከሁለት ዓመት በፊት የዓለም ጤና ድርጅት ባወጣው ጥናት በዓለም አቀፍ ደረጃ በ85 ሀገራት 627 ሺ ሰዎች በወባ በሽታ መሞታቸውን አስታውቋል።
በሰብ ሳህራ አፍሪካይህ በሽታ ክንዱን ከሚያበረታባቸው አህጉር ደግሞ አፍሪካን በዋናነት መጥቀስ ይቻላል። ከበሽታው አስከፊነት ባለፈ የአፍሪካ ሀገራት መድኃኒቱን ስለማያመርቱ ከሌሎች አምራች ሀገራት ነው የሚያስገቡት ይኽም ታዲያ ችግሩን ከባድ አድርጎታል።
አሁን ላይ ግን የዓለም ጤና ድርጅት በኩል የወጣው ዜና ተስፋን የሚጭር ኾኗል። በአፍሪካ የተመረ እና ለወባ በሽታ የሚውል መድኃኒት አረጋግጦ መጠቀም ይቻላል ሲል የሁይንታ የምስክር ወረቀት ሰጥቷል።
በኬኒያ ዩኒቨርሳል ኮርፖሬሽን በተባለ መድኃኒት አምራች ኩባንያ የተመረተው የወባ መድኃኒት ሱልፋዶክሲን ፒሪሚታሚን የሚል ስያሜን አለው። ይኽው መድኃኒት በዋናነት ለሕጻናትና ነብሰጡር እናቶች የሚውል ነው። እነዚህ ዜጎች ለወባ በሽታ በሰፊው የሚጋለጡ በመኾናቸው ነው መድኃኒቱ ለነሱ ይውላል የተባለው።
በአፍሪካ በዓመት ከ 50 ሚሊዮን በላይ ነብሰጦሮች እንደሚኖሩ የዓለም ጤና ድርጅት ገልጿል። እነዚህ ነብሰጦር ሴቶች ታዲያ ለዚህ በሽታ በከፍተኛ ኹኔታ ተጋላጭ እንደኾኑ ነው ድርጅቱ የገለጸው።
በተመሳሳይ በአፍሪካ በወባ ከሚሞቱት ሰዎች መካከል 80 በመቶ የሚሆኑት ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ናቸው።ይህ ግኝት በአፍሪካ ውስጥ ጥቅም ላይ የሚውሉ ጥራት ያላቸው መድኃኒቶች በአካባቢው ማምረት አስፈላጊ መሆኑን የሚያሳይ እና በር ከፋች ነው ተብሎለታል።
እንደአብነትም ከኹለት ዓመት በፊት የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በዓለም ላይ ከተከሰተ በኋላ አቅም ያላቸው ሀገራት የኮቪድ ክትባትን በገፍ ሲገዙ አሊያም ሲያመርቱ እና ሲጠቀሙ አፍሪካ ተመልካች ነበረች። ከቆይታ በኋላ ነበር ክትባቱን ማግኘት የቻለችው።
በአህጉሪቱ የተመረተው ሱልፋዶክሲን ፒሪሚታሚን የተሰኘው የወባ መድኃኒት ታዲያ አፍሪካ እንደምትችል ማሳያ ነው ተብሏል። ቢኾን ግን አሁንም ብዙ መሥራት እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።
በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ከምርት ጀምሮ እስከአቅርቦት የወባ መድኃኒት የማግኘቱ ላይ ችግሮች እንዳሉ ሲጂቲኤን በዘገባው አስፍሯል። በዚህም ምክንያት ጥራታቸው ያንያህል ጥሩ ባልኾኑና ከውጪ በሚገቡ መድሀኒቶች ጥገኛ እንደኾነው ተብሏል።
በወባ በሽታ ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ሀገሮች ተመራማሪዎችና አምራቾች በሽታውን ለማሸነፍ በሚደረገው ጥረት ግንባር ቀደም መሆን እንዳለባቸውም ተጠቁሟል።
ዩኒቨርሳል ኮርፖሬሽን የመድሀኒት አምራች ድርጅት በአፍሪካ የመጀመሪያው የወበ በሽታ የማምረት ፈቃድ የተሰጠው ድርጅት ነው።
በሙሉጌታ በላይ
2022-08-26