ሀገሬ ቲቪ

ካርታቸው የመከነባቸው 671 ይዞታዎች

በመዲናዋ በህገወጥ መንገድ የተወረሩ 671 ቦታዎች መገኘታቸው ተሰማ፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ ጀማል አልዬ 260ሺሕ 106 ካሬ ሜትር ይዞታዎች ወደ መሬት ባንክ መመለሳቸውን ተናግረዋል፡፡ በህገወጥ ወረራ የተያዙት ቦታዎች ካርታቸው ሙሉ በሙሉ ተቀምቷል፡፡ 88 አመራሮችና ሰራተኞች ከሥራ ገበታቸው ታግደዋል፤ ጉዳያቸውም በፍርድ ቤት መያዙ ተገልጿል፡፡ የመሬት ወረራን ለመከላከል እና ለመቀልበስ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ግብረ ሀይል መቋቋሙ ይታወሳል፡፡ የመንግስት ትኩረት በሰሜኑ ኢትዮጵያ ባለው ጦርነት ላይ ነው በሚል መሬትን በህገወጥ መንገድ ለመውረር የሚደረግ ጥረት በታሪክ ያስጠይቃል ተብሏል፡፡ ህገ ወጥ ወረራ በስፋት የተስተዋለባቸው ለሚ ኩራ፣ ቦሌ፣ አቃቂ ቃሊቲ እና ንፋስ ስልክ ክፍለ ከተሞች ናቸው፡፡ ኃላፊው ህገ ወጥ መሬቱን ገቢ ስናደርግ ጥቂት ደላሎችና ግለሰቦች ህጋዊ ግለሰቦች ተጎድተዋል የሚል ወሬ በመንዛት ስራችንን ሊያስተጓጉሉ ሞክረዋል ብለዋል፡፡ ያለአግባብ መሬት እንዲወረር የፈቀዱ ጥቂት የመዲናዋ የደንብ ማስከበር ባለሙያዎች ተጠያቂ እየተደረጉ መሆናቸው ተመላክቷል፡፡ ህብረተሰቡም መሬት ሲሸጥ ሲለውጥ ወደ መዲናዋ የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ በመቅረብ ስለህጋዊነቱ መጥየቅ ይኖርበታል መባሉን ሰምተናል ፡፡

በሀገሬ ቲቪ
2021-12-28