የ2014 ዓ/ም የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ከመስከረም 30 እስከ ጥቅምት 11 ቀን 2015 እንደሚሰጥ ተነግሯል። ይህ የፈተና ፕሮግራም ከሌላው ጊዜ የተለየ የሚያደርገው በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አሊያም በዩኒቨርሲቲ እንዲሰጥ መወሰኑ ነው።
አሁን ላይ ሁሉም ዩኒቨርትስቲዎች ግብረኃይል አቋቁመው በዝግጅት ላይ እንደኾኑ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ምክትል ኃላፊ አቶ ይልቃል ወንድሜንህ ለጣቢያችን ተናግረዋል።
ተፈታኝ ተማሪዎች መደበኛ ተማሪዎች ሲያገኙ የነበሩትን አገልግሎቶች በመንግሥት በሚሸፈን ወጪ ያገኛሉ ብለውናል። መስከረም 30 2015 የሚጀመረው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና አሁን ላይ የፈተናው የኀትመት ሥራዎች እየተጠናቀቀ ነው ተብሏል።
ሁሉንም ተማሪዎች በአንድ ላይ መፈተን አስቸጋሪ ስለሚኾን ፈተናው በሁለት ዙር እንደሚሰጥ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት አሳውቋል።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሌሉባቸው ዞኖች እና ከተማዎች የሚገኙ ተፈታኝ ተማሪዎችን እንዴት ልታስተናግዷቸው አስባቹኋል ብለን ለጠየቅነው ጥያቄ ከፍተኛ ትምህርት ወደሚገኙባቸው አካባቢዎች እንዲሔዱ እና እንዲፈተኑ ይደረጋል ሲሉ አቶ ይልቃል ወንድሜንህ ገልጸዋል።
በተለያዩ ጊዜአት እየታየ ያለውን የፈተና ስርቆት ለማስቀረት ሲባል ፈተናውን በነዚህ የትምህርት ተቋማት መስጠት እንዳስፈለገ ነው የተነገረው።
ከዚህ በፊት የነበረው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና አሰጣጥ ፈተናው ከታተመ በኋላ በሀገሪቱ የተለያዩ የመፈተኛ ማዕከላት እንዲሰራጭ ይደረግ ነበር በዚህ ሒደት ውስጥ ይፈተናው ደኀንነት ለአደጋ የተጋለጠ እንዲኾን ያደርገው ነበር ያሉት አቶ ይልቃል፤ አሁን ግን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፈተናው እንዲደረግ መወሰኑ ይህን ሥጋት የሚያስወግድ ነው ብለውናል።
በአጠቃላይ ከ900 ሺህ በላይ ተማሪዎች የ 2014 የ 12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን እንደሚወስዱ ይጠበቃል።
በሙሉጌታ በላይ
2022-08-29
