ዓላማችንን ከሚፈትኑ ነገሮች መካከል ዋነኛው ሌብነት ነው፤ በወል መጠሪያው ደግሞ ሙስና። ከድሆች ጉሮሮ መንጠቅ፣ በሌሎች ህልውና ላይ መፍረድም ጭምር ነው ይህ የሌብነት ተግባር።
ታዲያ ዓለማችን በዚህ የሌብነት ተግባር ብቻ 3.6 ትሪሊዮን ዶላሮችን ትሰረቃለች። ይህ እየመረረንም ቢሆን የምንውጠው የዓለማችን ሀቅ ነው።
በዚህ ሌብነት ላይ ህንድ ወሰደች የተባለችው እርምጃ በርካቶችን አስገርሟል። በህንዷ ኒው ዴልሂ አቅራቢያ ሰማይን ታከው ተገንብተው የነበሩ ፎቆች በሙስና የተገነቡ በመሆናቸው እንዲፈርሱ ተደርገዋል።
ሕንፃው 103 ሜትር ርዝማኔ ያለው ባለ 32 ወለል ለመኖሪያ ያገለግል የነበረ ሕንፃ ነው። ታዲያ የዚህ ሕንፃ ነበር መሰኘት ምክንያቱ ሙስና ነው፤ ሌብነት።
ለረዥም ወራት በፍርድ ቤት ክርክር ላይ የነበረው ይህ ሕንፃ የህንድ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሕንፃው ከዚህ በላይ በህይወት ሊቆም አይገባውም መፍረስ አለበት ሲህ ውሳኔውን አሳልፏል።
ፍርድቤቱ በርካታ የሕንፃ ግባታ ህጎችን እና የእሳት አደጋ መከላከያዎችን ሳያሟላ በዘፈቀደ የተገነባውን ሕንፃ ዳግም እንዳላየው ብሏል።
የሕንፃው ገንቢዎች ግንባታውን ባደረጉበት ሰዓትም በአካባቢው ካሉ የቤት ገንቢዎች ጋር ሊኖራቸው የሚገባውን ስምምነት አላደረጉምም ብሏል።
ገንቢዎቹ ታዲያ ይህንን ሁሉ የህግ እና የስርዓት ጥሰት ለመፈፀም ደግሞ ሀይ ባዮቹን አፋቸውን በብር አበስ አድርገዋል ነው የተባሉት።
የህንድ ፖሊስም በተባለው መንገድ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ዝንፍ ሳያደርግ ፈፅሞታል። ለመገንባት ዓመታትን የፈጀውን የሙስና ሕንፃ በ10 ሴኮንዶች ውስጥ ታሪክ አድርጓቸዋል።
እነዚህን መንትያ ሕንፃዎች ከአፈር ለመደባለቅ ከ3,700 ኪ.ግ በላይ ፈንጂዎች ጥቅም ላይ ስለመዋላቸውም ተሰምቷል።
“ሁሉም ነገር በሚገባው ነው የተደረገው፤ የፍርድቤቱን ትዕዛዝ ተከትለን በሚገባ ፈፅመናል።”
በስፍራው የነበሩ አንድ የፖሊስ አዛዥ ሕንፃው ከፈረሰ በኋላ የተናገሩት ነበር። መቼም ይህንን የሚያክል ሕንፃ እንዲፈርስ ሲደረግ የሚነሳው አቧራ ቀላል የሚባል አይደለም።
ለዚህም ሲባል በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከመኖሪያቸው እንዲርቁ ተደርገው ነበር። በዙሪያው ላሉ ሕንፃዎችም ቢሆን አቧራው ጉዳት እንዳያደርስባቸው ህንዳውያኑ መላውን ዘይደዋል።
ሕንፃዎቹን በላስቲክ መሰል ነገር መሸፈን። በቦታው ላይ የሚነሳውን አቧራም ለመቀነስ የውሃ መርጫ መሳሪያዎች ጥቅም ላይ መዋላቸውን ስካይ ኒውስ አስነብቧል።
ይህ ሁሉ ታዲያ ሙስና ይሉት ሌብነት አካል ነስቶ ቆሞ እንዳይታይ ማድረጊያ ነው። ምን አለ ሁሉም ጋር እንዲህ ቆራጥ አንጀት በኖረ አያሰኝም?
በሳምሶን ገድሉ
2022-08-29
