በንፋስ ስልክ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ጀሞ አንድ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ በ63 ሚሊዮን ብር ወጪ ከስምንት ወራት በፊት የመንገድ ሥራ ፕሮጀክት ተጀምሮ ነበር። ይኸው መንገድ 1.6 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ አለው።
ይሁን እንጂ ለመንገድ ሥራው ታስቦ የተቆፈረው ጉድጓድ በክረምቱ ወራት በጣለው ዝናብ በውኃ ተሞልቶ ሰዎችን ለአደጋ እያጋለጠ መኾኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ነግረውናል።
እነዚህ ነዋሪዎች ሁኔታውን ለክፍለከተማ እና ወረዳው ከማሳወቅ አንስቶ በራሳቸው አቅም የታቆረው ውኃ እንዲፈስ ለማድረግ መከራ አድርገው እንደነበር ነግረውናል ነገር ግን እስካሁን ድረስ ዘላቂ መፍትሔ ማግኘት እንዳልቻሉ ነው የነገሩን።
አፍሪካ ሕንፃ ጀሞ መስታዎች ፋብሪካ የሚል ስያሜ ያለው የመንገድ ፕሮጀክት በ2015በጀት ዓመት ሰኔ ወር እንደሚጠናቀቅ አ.አ መንገዶች ባለሥልጣን የኮንስትራክሽን ሥራዎች ቡድን መሪ ኢንጂኒየር አንተነህ ግርማ ነግረውናል።
አሁን ላይ መንገዱ 76 በመቶ መጠናቀቁንም ነግረውናል። የአካባቢው ነዋሪዎች ያነሱት ጥያቄ የሚቀበሉት መኾኑን ገልጸው የዋናው መንገድ ውኃ ማስተላለፊያ ትቦ እና የአዲሱ መንገድ ትቦ መጠን መለያየት ችግሩ እንዲከሰት አድርጎታል ብለውናል።
ይህ ችግር ከታወቀ አንስቶ የተለያዩ የመፍትሔ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ኢንጂኒየር አንተነህ ግርማ ነግረውናል።
አሁን ላይ ግን ዘላቂ መህትሔ ኾኖ የተወሰደው የፍሳሽ ማስተላለፊያውን ቱቦ መጠን መሉ ለሙሉ መጠኑ ከፍ ወዳለው ቱቦ እንዲለወጥ ማድረግ ነው ብለውናል። ይህንን ሥራ በአስቸኳይ እንዳንከውን በቅድሚያ መጠናቀቅ ያሉባቸው ጉዳዮች ስላሉ መኾኑንም ገልጸዋል።
በሚቀጥሉት 15 ቀናቶች ውስጥ እንደዘላቂ መፍትሔ የተያዘውን የፍሳሽ ማስተላለፊያ የመቀየር ሥራው ይጀመራል ተብሏል።
በሙሉጌታ በላይ
2022-08-30
