ሆ ቺ ሚን በቬትናም የትግል እንቅስቃሴ ውስጥ ስሙ ጎልቶ የሚነገር ታጋይ ነው። በኛም ሀገር ቢሆን ‘’ ፋኖ ተሰማራ ፋኖ ተሰማራ፤ እንደ ሆቺ ሚኒ እንደ ቸጉ ቬራ። ‘’ የተባለለት ነው። ለዛሬ ሆቺ ሚንን እናስታውሰዋለን።
በቬትናም ጦርነት የሆች ሚን ተሳትፎ ትልቅ ነበር። ይህ ሰው ታዲያ በጊዜው የደቡቡን የኮሪያ ክፍል ይዛ ትዋጋ ከነበረችው አሜሪካ ፕሬዝዳንት ኒክሰን ለተላከለት ደብዳቤ የአሜሪካን በሀገሪቱ እያደረገችው ያለው ጦርነትን ወረራ ነው፤ ቬትናምን ለቬትናማውያን ተይ ሲል ምላሽ የሰጠው በዛሬዋ ዕለት በ1961 ዓ.ም. ነበር።
የጸረ ቅኝ ግዛት እንቅስቃሴን በመምራት ብሎም ለሀገሩ ነጻነት በመታገል ስሙ የሚጠቀስ ሰው ነው፤ ሆ ቺ ሚን። ሆ ቺ ሚን የተወለደው የፈረንሳይ ኢንዶቻይና ተብላ ትጠራ በነበረችው ሆንግ ትሩ በቬትናም በ1882 ዓ.ም. ነበር። ይሄው ሰው የኢንዶቻይና ኮሚዩኒስት ፓርቲ መስራች ብሎም የሰሜን ቬትናም መሪ በመሆን ለ24 ዓመታት ያገለገለ ሰው ነው።
የቬትናም ብሄራዊ እንቅስቃሴ መሪ ሆኖ ለ30 ዓመታት ሲቆይም ሆ ቺ ሚን በኤስያ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የጸረ ቅኝ ግዛት እንቅስቃሴዎችን የመራ የ20ኛው ክፍለ ዘመን ተጽዕኖ ፈጣሪ የኮሚዩኒስት መሪ ነው።
ልጅነቱን በቬትናም ማሳለፍ የጀመረው ሆ ቺ ሚን ጥቂት ትምህርትን በዚያው መከታተል ጀምሯል። ኋላም ለፈረንሳዊ ሰው ምግብ አብሳይ ሆኖ ተቀጠረ።
ለሶስት ዓመታትም በባህር ላይ ስራ ቆይቷል። የአፍሪካ ወደቦችን እና የአሜሪካ ከተሞችን መጎብኘት ችሏል። በለንደን ለሁለት ዓመታት የኖረው ሆቺ ሚን ኋላም ወደ ፈረንሳይ በመጓዝ እንደ አትክልተኛ፣ አስተናጋጅ የመሳሰሉ ስራዎችን ሰርቷል።
ለስድስት ዓመታት በፈረንሳይ በደረገው ቆይታም ንጉየን ሃገር ወዳዱ በሚል ስም ንቁ ሶሽያሊስት ሆኗል። በዚያ የሚኖሩ ቬትናማውያንን በማስተባበርም ባለ ስምንት ነጥብ ቅሬታን ለአንደኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ የቨርሳይለስ የሰላም ውይይት ተወካይ መሪዎች ልኮ ነበር።
በቅሬታው ሆ በቬትናም እና ኢንዶቻይና ቀጠና የነበሩ የፈረንሳይ ቅኝ ገዥዎች ለሚገዡቸው የአካባቢው ሰዎች እኩል ስልጣን እንዲሰጡ ፍላጎት ነበረው። ምንም እንኳን የሰላም ተሰብሳቢ ነን ያሉት ለቅሬታው መልስ ባይሰጡም ሆ ቺ ሚን ፖለቲካዊ ንቃት በነበራቸው ቬትናማውያን ጀግና እንዲባል አድርጎታል።
በቀጣዩ ዓመት በሩስያ ስኬታማ አብዮትን የኮሚዩኒስት ፓርቲ ማድረጉን እና የቭላድሚር ሌኒንን ጸረ ኢምፔርያሊስት አቋም የተመለከተው ሆ ቺ ሚን የፈረንሳይ ኮሚዩኒስት ፓርቲን ተቀላቀለ።
በፈረንሳይ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ በተሳተፈበት ከሰራተኛው መደብ መሪዎች ጋር ከተዋወቀ በኋላ ወደ ሞስኮ አምርቷል። የፈረንሳይ ኮሚዩኒስት ፓርቲን ቅኝ ግዛትን የሚያወግዝ አለመሆኑንም ይተች ነበር።
በ1910ዎቹ አጋማሽ የቬትናም ብሄራዊ እንቅስቃሴን አደራጀ። የቬትናም አብዮታዊ የወጣቶች ማህበርንም አቋቋመ። ብዙዎቹ አባላቶቹ ከኢንዶቻይና በነበራቸው የፖለቲካዊ አመለካከት የተሰደዱ ነበሩ።
በሀገራቸው የነበረውን የፈረንሳይ አገዛዝ የመቃወም ፍላጎት የነበራቸው ናቸው። ማህበሩ የኢንዶቻይና ብሄርተኝነት ማቀንቀኛ ሆነ። ሆ ቺ ሚን ደግሞ የዚህ እንቅስቃሴ መሪ።
በሆንግ ኮንግ ደግሞ የኢንዶቻይና የኮሚዩኒስት ፓርቲ እንዲቋቋም አደረገ። በቬትናም ከተሞች ደግሞ ንቁ ቅርንጫፍ እንዲኖረው ተደረገ። ገዥ የነበረችው ፈረንሳይ ለማህበሩ የምትሰጠው ምላሽ የከፋ ነበር። ሆ ቺ ሚንም ቢሆን በሌለበት የሞት ፍርድ ተበይኖበታል።
ሆ ቺ ሚን እና ወታደራዊ መሪዎቹ ከሶቭየት እና ቻይና ጋር ግንኙነት ያደርጉም ነበር። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ፈረንሳይ በጀርመን ስትሸነፍ ቬትናም ነጻ ባትወጣም የቻይና መንግስት ግን በኮሚዩኒስትነቱ ጥርጣሬ ስላደረበት ለ18 ወራት አስሮታል። በእስር ሳለም ግጥሞቹን ፍልስፍናዎቹን መጻፍ ችሏል። የትግል ጓዶቹ ግን በድርድር አስፈትተውታል።
የመሰረተው የኮሚዩኒስት ፓርቲ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ሰፊ ድጋፍ ማግኘት ችሏል። የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኦፍ ቬትናምን በመምራትም የፈረንሳይን ህብረት በ1946 ዓ.ም. አሸንፏል። ይሄው ክስተት የቬትናምን መከፋፈል አምጥቷል።
የኮሚዩኒስት ክንፉን በመምራትም የሰሜን ቬትናም መሪ ሆኗል። ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ የደቡቡን ክፍል ካፒታሊስት ክንፍ በመደገፍ ብትዋጋም የሰሜኑን የቬትናም ክፍል ማሸነፍ አልተቻላትም።
ሆ ቺ ሚንም ምንም እንኳን ቬትናምን ወደ አንድ ማምጣት ባይቻለውም ለቬትናም ነጻነት ባደረገው ጠንካራ ትግል የሚታወስ ሰው ሆኗል። በቬትናም ጦርነትም ጠንካራ መሪ ሆኖ ቀጥሏል።
ገጣሚ፣ ጸሃፊ፣ ፖለቲከኛ፣ ታጋይ የሆነው ሆ ቺ ሚን በጤና ሁኔታው ሳቢያም ከስልጣን ከወረደ ከአራት ዓመታት በኋላ በ1962 ዓ.ም. አርፏል። ቬትናምም ከሞቱ ከሰባት ዓመታት በኋላ እንደገና ተዋህዳለች።
በአብርሃም በለጠ
2022-08-30
