ሀገሬ ቲቪ

ከ67 ዓመታት በፊት የተሰራው የፀሃይ ኃይል መኪና

ዛሬ ላይ የመኪና ቴክኖሎጂ እየተሻሻለ መጥቶ በየጊዜው ለውጦች የሚደረጉበት ሆኗል። ከኃይል አጠቃቀም አንጻርም የአየር ብክለትን ለመቀነስ የኤሌክትሪክ መኪኖችን ማምረት የሚመከር ከሆነ ሰነባብቷል።

እንደፀሃይ ኃይል ያሉ ታዳሽ ኃይሎችን መጠቀም ደግሞ የሚበረታታ ሆኗል። 67 ዓመታትን ወደ ኋላ መለስ ስንል የመጀመሪያዋ የፀሃይ ኃይል የምትጠቀም መኪና የተሰራችው በዛሬዋ ዕለት ሆኖ አገኘነው። የዕለቱን ከታሪክ ትኩረታችን ነው።

በጀርመኑ ኢንጂነር ካርል ቤንዝ የመጀመሪያዋ ነዳጅ የምትጠቀም መኪና ከተዋወቀች ግማሽ ክፍለ ዘመን አልፏል። ግዜው የ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ነው፤ 1947 ዓ.ም. ።

ዊልያም ኮብ የተባለ ሰው የመጀመሪያዋን በፀሃይ ኃይል የምትሰራ መኪና ይፋ አደረገ። ይህችው የፀኃይ ኃይልን የምትጠቀመው ሰንሞባይል (Sunmobile) ተሽከርካሪ በመጠን ትንሽ ነበረች።

የጀነራል ሞተርስ ባልደረባ የሆነው ዊልያም ኮብስ ሰንሞባይል የተሰኘችውን ተሽከርካሪ ያስተዋወቀው በጄነራል ሞተርስ የፓወራማ የተሽከርካሪ ትርኢት ላይ በአሜሪካ ቺካጎ፣ ኢሊኖይስ ነው።

ይህችው በዓይነቷ የመጀመሪያ የሆነችው መኪና የፀሐይ ብርሃንን በነዳጅ ምትክ የምትጠቀም ነበረች።

ለአንድ ወር ያህል በቆየውና 7 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚያህል ግምት ባለው የፖወራማ የጀነራል ሞተርስ ትርኢት ከተማ በ250 የሚያክሉ ነፃ ኤግዚቢሽኖች መካከል ነው የወደፊት (futuristic) የተባለላት ሰንሞባይል መኪና የቀረበችው።

ከኮብ ትንሽ አውቶሞቢል በተጨማሪ የፖወራማ ጎብኚዎች ከዘይት ጉድጓዶችና ከጥጥ ጅኖች አንስቶ እስከ ባሕር ሰርጓጅ መርከቦችና ሌሎች ወታደራዊ መሣሪያዎች እንዲጎበኙ ተደርገዋል።

በዚህ ውስጥ ግን የመጀመሪያዋ በፀሐይ ኃይል የምትሰራ አነስተኛ ተሽከርካሪ ትኩረትን መሳቧ አልቀረም። በመጠኗ ትንሽ መሆኗ ግን ለመንዳት ምቹ እንዳትሆን ያደርጋታል።

ምንም እንኳን የጸሐይ ኃይልን የምትጠቀም ተሽከርካሪን ከ67 ዓመታት በፊት ዊልያም ኮብ በማምረት በኩል ዓይንን መግለጥ ቢችልም የፀሐይ ኃይልን መጠቀም የተሽከርካሪ ኢንዱስትሪውን ዘርፍ የመቀየር አቅም የነበረው ቢሆንም ብዙ አልተገፋበትም። ኮብ ግን የመጀመሪያውን ሰንሞባይል የተሰኘችውን ተሽከርካሪ በማምረቱ ስሙ ይወሳል።

ዛሬ ላይ ግማሽ ክፍለ ዘመን አልፏል። ለኃይል ምንጭነት የፀሐይ ብርሃንን የሚጠቀሙ መኪኖች ይመረታሉ። ግና ደግሞ በየትኛውም ገበያ ላይ አልዋሉም። ግና ደግሞ የፀሐይ መኪኖች ውድድር ይካሄዳል።

ፎቶቮልታይክ (PV) የተሰኘ ስያሜ ያልቸው እነዚህ ተሽከርካሪዎች ርስበርሳቸው እንዲፎካከሩ ይደረጋል። የፀሐይ መኪኖችን የሚያመርቱ እንደጃፓኑ ቶዮታ ሞተርስ ያሉ በሰፊው ይንቀሳቀሳሉ። ግን ደግሞ ርስ በርስ ለመፎካከር ከመሆኑ ባሻገር ተደራሽ አላደረጉትም።

በአብርሃም በለጠ
2022-08-31