ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቼስኮስ በጣሊያን የዉልደት መጠን መቀነስ አሳሳቢ ነው አሉ፡፡ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በጣሊያን አዲስ የሚወለዱ ህጻናት ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ማሽቆልቆሉ ለሀገሪቱ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ስጋት መሆኑን አስጠንቅቀዋል፡፡ ጣሊያን በፈረንጆቹ 1861 እንደ ሀገር ከተዋሀደች በኋላ ዝቅተኛው የወሊድ መጠን ባለፈዉ ዓመት መመዝገቡን የብሔራዊ ስታቲስቲክስ ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡ ባለፉት 12 ዓመታት በተከታታይ የወሊድ መጠን በሀገሪቱ እየቀነሰ መምጣቱ ተሰምቷል፡፡ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በቅዱስ ጴጥሮስ ቤተ ክርስቲያን ፊት ለፊት ባደረጉት ሳምንታዊ ንግግራቸው በጣሊያን የወሊድ መጠን መቀነስ በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ገልጸዋል፡፡ በርካታ ሰዎች ልጅ የመውለድ ፍላጎታቸው የጠፋ ይመስላል፤ ልጅ ሳይወልዱ ወይም አንድ ልጅ ብቻ መውለድን ይመርጣሉ። ይህ አሳዛኝ ነገር ነው ከወደፊት የጣሊያን ተስፋ ጋር ይጋጫልም ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ በጣሊያን ባለፈው ዓመት 404ሺሕ 892 ህጻናት መወለዳቸዉ ተነግሯል፡፡ እንደ ጣሊያን የብሄራዊ ስታቲስቲክስ ጽህፈት ቤት መረጃ ከሆነ ከ2019 ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ15ሺሕ የ2020 ዓመት የወሊድ መጠን መቀነሱን ያሳያል፡፡ በ2020 ዓመት በጣሊያን 404ሺሕ ህጻናት መወለዳቸዉ ሪፖርት ቢደረግም ከ746ሺሕ በላይ ሰዎች በኮቪድ ህይወታቸዉን አጥተዋል፡፡ በጣሊያን በዓመት ዉስጥ ከሚወለዱ ህጻናት ቁጥር እጥፍ አዋቂዎች በኮቪድ-19 ምክንያት ህይወታቸዉን እያጡ ነው፡፡
በሀገሬ ቲቪ
2021-12-28
