ከመበታተን አንድ መሆን ምን ማለት እንደሆነ ለዓለም ማሳያ ነች። 7 የበረሀ ሀገርት በጋራ መጠሪያቸው የተባበሩት አረብ ኤመሬቶች።
ዓለም በአንድነት ወደ እነዚህ ሀገራት ለተለያዩ ምክኒያቶች ይተማል፤ ዛሬ በበረሀው ላይ ሌላ አዲስ ዓለም አለና ነው።
ከኤሜሬቶች መካከል ዱባይ ትልቋ የቱሪስት ቀልብ ማሳረፊያ ናት። ይህች የበረሀ ገነት ከራሷ ባልሆኑ ከሌላ አካባቢ በመጡ አሸዋ እና ድንጋይ ላይ የታነፀች ከተማ ነች።
ታዲያ ይህችው ከተማ ዓለምን ጉድ ያሰኙ በሰው እጅ የተሰሩ ያማሩ ደሴቶች መገኛም ጭምር ነች። አሁን ደግሞ እየገነባች ያለችው አዲሱ መዝናኛ ሊገባደድ እንደሆነ ተሰምቷል።
ወደ 5 ቢሊዮን ዶላር ወጪ የተደረገበት እና በባህርላ በሰው በተሰሩ ደሴቶች ላይ እየተገነባ ያለው መዝናኛ አሁን የመጀመሪያው ምዕራፍ ስለመገባደዱ ይፋ ተደርጓል።
ይህ ለ ሁለት አስርት ዓመታት በስራ ላይ የነበረው ትንሿን አውሮፓ በባህሩ ላይ መስራት አሁን እውን እየሆነ ነው። ዱባውያኑ በባህሩ ላይ ወደ 300 የሚጠጉ ደሴቶችን አሳምረው አበጅተዋቸዋል።
ከዋናው መሬት 4 ኪሎ ሜትሮን በጀልባ ከተጓዙ በኋላ የሚገኙት እኚህ 300 የሚደርሱ በሰው እጅ የተፈጠሩ ውብ ደሴቶች ከ1995 ዓ.ም. ፕሮጀክቱ ከተጀመረ ጀምሮ ሰው ድርሽ ሳይልባቸው ባዷቸውን የነበሩ ናቸው።
በእነዚህ ደሴቶች ላይ ከ15 ያላነሱ ቅንጡ ሆቴሎች፣ የቫኬሽን ማረፊያ ቤቶች እና ለቢሊየነሮች የተዘጋጁ መኖሪያዎች አልቀው መታየት ጀምረዋል።
ግንባታቸው ተተናቆ ክፍት የሆኑት 6 ደሴቶች የአውሮፓ ልብ የሚል ስያሜን ይዘዋል። ታዲያ ተጓዦች በደሴቶቹ ውስጥ እንደ ስዊድን፣ ጀርመን፣ ስዊዘርላንድ፣ ቬኒስን እና ሌሎችን የአውሮፓን ክፍል በትንሹ እንዲደግሙ ታስበው ከተዘጋጁ ስፍራዎች መምረጥ ይችላሉ ተብሏል።
በደሴቶቹ ላይ የተዘጋጁት ቦታዎች አየር ንብረታቸው ሳይቀር ከአውሮፓ ጋር እንዲመሳሰል ስለመደረጉም ሲኤን ኤን አስነብቧል።
በዚያ በርሃ መሃል የበረዶ ግግር ሳይቀር በአውሮፓ ውስጥ እንደሚመለከቱት ተቆልሎ ያገኙታል።
በባህሩ ላይ የተዘጋጁት ቤቶች ከባህር በታች ያለውን ሁኔታ መመልከት በሚያስችል መልኩ የተዘጋጁ ስለመሆናቸውም ተሰምቷል።
ብቻ ምን አለፋዎች ዓለምን በአንድ ላይ ጠቅልሎ ያሳያል የተባለው የዱባይ ፕሮጀክት አሁን ለጎብኚዎች ክፍት እየሆነ ነው።
ለመልካም ሀሳብ የተሰባሰቡ ልባሞች ያቆሟት ሀገር ዛሬ ዓለምን በውስጧ ታቅፋለች።
ከስሪቴም፤ ከስራዬም ተማሩብኝ እያለች ትገኛለች። ልባም ከሞኝ ብቻም አይደለም ከልባምም ይማራል እና።
በሳምሶን ገድሉ
2022-08-31
