ሙአመር ጋዳፊ በሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር ሊቢያ አብዮት እንደጀግና የሚታይ መሪ ነበር። ይህ ሰው ብዙ ደም አፋሳሽ ባልሆነ መንገድ ነበር የሊቢያን ስልጣን የተቆናጠጠው።
የ27 ዓመቱ የጊዜው ኮሎኔል ጋዳፊ በዛሬዋ ዕለት ነበር በ1961 ዓ.ም. የሀገሪቱ መሪ የነበሩትን ንጉስ ኢድሪስን ከስልጣን በመፍንቅለ መንግስት እንዲወርዱ ያደረገው። የዕለቱን ከታሪክ ትኩረት ነው።
53 ዓመታትን ወደ ኋላ መለስ ብለን ታሪክን ልንቃኝ ሰሜን አፍሪካ ሊቢያ ደርሰናል። የሊቢያ ጦር አዛዥ የነበረው ኮሎኔል ሙአመር አል ጋዳፊ የሊቢያን አብዮት በመምራት ላይ ነው። የጊዜው ንጉስ ኢድሪስ በዙፋኑ ላይ እንዲቆዩ ምቹ ሁኔታ ያለ አይመስልም።
ወጣቱ እና የ27 ዓመቱ ኮሎኔል ጋዳፊ የተሳካ መፈንቅለ መንግስትን በዛሬዋ ዕለት በ1961 ዓ.ም. በንጉስ ኢድሪስ ላይ አደረገ። ንጉስ ኢድሪስ በወታደራዊ መፈንቅለ መንግስቱ ከስልጣናቸው ሲወርዱ የሊቢያ ጦር አዛዡ ጋዳፊ አዲሱ የሊቢያ መንግስት ሊቀመንበር እና የአብዮታዊ ምክር ቤት መሪ ተባለ።
በሊቢያ አብዮት ውስጥ እንደጀግና የሚታየው ሙአመር አል ጋዳፊ የተወለደው በሊቢያ በርሃ በ1934 ዓ.ም. ነው። የገበሬ ልጅ የነበረው ጋዳፊ ጎበዝ ተማሪ የነበረ ሲሆን ከሊቢያ ዩኒቨርሲቲ ብሎም ከሊቢያ ወታደራዊ አካዳሚ በ1950ዎቹ አጋማሽ ተመርቋል።
ጠንካራ የአረብ ብሄርተኝነት የነበረው ጋዳፊ የሀገሪቱ መሪ የነበሩትን ንጉስ ኢድሪስን ከስልጣን ለማውረድ ከሌሎች ባለስልጣናት ጋር አሴሯል።ንጉሥ ኢድሪስ በአረብ አገሮች መካከል የበለጠ ፖለቲካዊ አንድነት ለማምጣት ለተደረገው እንቅስቃሴ ከልክ ያለፈ ወግ አጥባቂና ግድ የለሽ እንደሆኑ ተደርጎ ይታዩ ነበር።
በጊዜው ደግሞ የሊቢያ ወታደራዊ አካዳሚ ምሩቅ የነበረው ጋዳፊ በ1961 ዓ.ም. የአዛዥነት ስልጣን ላይ ሲደርስ በሀገሪቱ የነበሩት አብዮተኞች ንጉስ ኢድሪስ ላይ ያላቸውን የተቃውሞ እንቅስቃሴያቸውን አጠናክረዋል።
አብዮተኞቹ ንጉሱ ከሀገር እስኪወጡ እየተጠባበቁ ነበር። ንጉሱ ለህክምና ወደ ቱርክ ሲያቀኑ ያለደም መፋሰስ የመፈንቅለ መንግስት እንቅስቃሴ አደረጉ። የሊቢያ ንጉሳዊ አገዛዝ ተወገደ።
የመፈንቅለ መንግስቱ መሪ ግን ወጣቱ ጋዳፊ ነበር። ንጉስ ኢድሪስ ስልጣናቸውን ወደ ቱርክ እንደተጓዙ ከተነጠቁ በኋላ የግብጽን ጥገኝነት ከማግኘታቸው አስቀድሞ ከቱርክ ወደ ግሪክ ተጉዘዋል። በዚያው በግብጽ ካይሮም በ1975 ዓ.ም. አርፈዋል።
ጋዳፊ እስላማዊ ስርዓትን፣ አብዮታዊ ሶሻሊዝምን እና የአረብ ብሔርተኝነትን በማዋሃድ በሊቢያ የፀረ-ምዕራባውያን አቋም ያለው ስርዓት አቋቁሞ ነበር።
የሊቢያን የመሪነት ስልጣን ከተቆናጠጠ በኋላ የዩናይትድ ስቴትስንና የብሪታንያን ወታደራዊ ጦር ሰፈሮች አስወግዶ ጣሊያናውያንንና አይሁድ ሊቢያውያንን አባረረ። በሂደትም በውጭ አገር የተያዙ የነዳጅ ስፍራዎችን በቁጥጥሩ ስር አስገባ።
በባህላዊ የእስልምና ህጎች መሰረት እንደአልኮል መጠጣት እና ቁማር ያሉት እንዲከለከሉ አድርጓል። የሊቢያ ዜጎች የኑሮ ደረጃን የሚያሻሽሉ ማህበራዊ ፕሮግራሞችን በሰፊው አስጀምሯል።
ጋዳፊ የሊቢያ ዜጎች የኑሮ ሁኔታ እንዲሻሻል ከመስራቱ ባሻገር ጠንካራ የአረብ ብሄርተኝነት ስለነበረው የአረቡ ዓለምን አንድ ለማድረግ በነበረው ፍላጎት በአረቡ ሀገራት መካከል ጠንካራ ግንኙነት ለመፍጠር ፍላጎት ነበረው።
በተለይም ከሊቢያ ጎረቤት ግብጽ ጋር ጥብቅ ግንኙነት የመፍጠር ፍላጎት አሳይቷል። ይሁንና ግን ግብጽ እና ሌሎቹ የዓረብ ሀገራት ከእስራኤል ጋር ሰላማዊ ድርድር በመጀመራቸው የሊቢያ መገለል ከፍ ብሏል።
ጋዳፊ የሊቢያን የነዳጅ ሀብት በመጠቀም የሊቢያ ዜጎችን የኑሮ ሁኔታ አሻሽሏል። የጋዳፊ መንግስት በሽብርተኝነት የተፈረጁ እንደ የፍልስጤም ታጣቂዎች እና የፊሊፒንስ እስላማዊ አመጸኞችን መደገፉ ወትሮም ጥሩ ግንኙነት ካልነበረው ዩናይትድ ስቴትስ ጋር መቃቃር ውስጥ አስገብቶታል።
በ1970ዎቹ በአውሮፓ ለደረሱ ሽብር ጥቃቶች ምዕራባውያኑ ጣታቸውን ወደጋዳፊ መጠቆም ጀመሩ። በ1975 ዓ.ም. የአሜሪካ አየር ኃይል ሊቢያ ሽብርተኞችን እየደገፈች ነው በሚል በትሪፖሊ ላይ የአየር ጥቃት ማድረስ ጀመረ። የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም ቢሆን በሊቢያ ላይ ማዕቀብ ጥሎባታል።
ከአረቡ ዓለም የተነጠለው ጋዳፊ ከሌሎች እንደደቡብ አፍሪካ ያሉ የአፍሪካ ሀገራት ጋር ግንኙነት ለመምስረትም ጥረት አድርጎ ነበር። በ2003 ዓ.ም. በአረቡ ዓለም በነበረው ሰፊ አለመረጋጋት በሊቢያም በጋዳፊ መንግስት ላይ ተቃውሞዎች እንዲበራከቱ አድርጓል።
ይህም በአብዮተኞች እና ታማኞች መካከል በሊቢያ የርስ በርስ ጦርነት እንዲጀመር አድርጓል። በዚያው ዓመት የዩኤን የጸጥታው ምክር ቤት በጋዳፊ ላይ የአየር ጥቃት እንዲከፈት ወሰን። ወትሮም ቢሆን የጋዳፊን ውድቀት የሚመኙ ምዕራባውያን በኔቶ አማካኝነት የጋዳፊ ጦር ላይ የሃይል ክንዳቸውን አበረቱ ።
በዚህ ሳቢያ የሊቢያ አብዮት ጀግና በ42 ዓመታት የስልጣን ቆይታ የሊቢያን ዜጎች የኑሮ ሁኔታ ያሻሻለው ጋዳፊ ለመሽሽ ሲሞክር በውሃ መውረጃ ትቦ ውስጥ ተያዘ ።ኋላም ስለመገደሉ የሊቢያ ጊዜያዊ አስተዳደር አስታውቋል።
በአብርሃም በለጠ
2022-09-01
