የመካከለኛው ምስራቅ ዓለም ለሴቶች እምብዛም የተመቸ አይደለም ይባልለታል። በዚያ ሴቶች በበርካታ ማዕቀቦች ውስጥ የመኖር ግዴታ አለባቸው።
ምናልባትም በዚህ ዘመን እንዲህም አለ እንዴ የሚያሰኙ በርካታ ደንቦች እና ግዴታዎች በዚያ አሉ።
እንደ አፍጋኒስታን ባሉ ሀገራትም ሴቶች ከአንድ ወንድ ዘመዳቸው ጋር ካልሆነ በስተቀር ራቅ ወዳለ ቦታ መሄድ ህልም ነው። በኢራንም ሴቶች በርከት ያሉ ማዕቀቦች አለባቸው ከፍጋኒስታኑ ጋር ባይወዳደርም።
አሁን ግን ለኢራናውያን ሴቶች አዲስ ቀን እየወጣላቸው ይመስላል። ለ40 አመታት ተከልክለው ከነበረው ስታዲየም እንዲገቡ ተፈቅዶላቸዋል።
የወንዶቹን የእግር ኳስ ጨዋታ ስታዲየም ገብተው መከታተል እንዲችሉ። የሀገሪቱ የወጣቶች ጉዳይ እና ስፖርት ሚኒስቴር 28 ሺሕ የሚደርሱ ትኬቶችን ለሴት ተመልካቾች ለመሸጥ መዘጋጀቱን አወጀ።
የኢራን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር አህመድ ቫሂዲም እንዲህ አሉ፤ ስታዲየሞቻችንን ለሴቶች የኳስ ተመልካቾች ዝግጁ አድርገናል።
ባለስልጣናቱ በቂ ናቸው ያሏቸውን 500 ሴቶች ብቻ ለመጀመሪያ ጊዜ ጨዋታን እንዲመለከቱ ፈቀዱ። እነዚህ ሴቶችም በሰማያዊ እና በነጭ እንዲሁም በቀይ ቀለም አምረው በስቴዲየሙ ታደሙ።
አንዳንዶቹ በጉንጮቻቸው ላይ የሚወዱትን ክለብ አርማ እና የሚያደንቁትን ተጫዋች ተሳሉ። በኳስ ፍቅር የወደቁት እነዚህ የኢራን ሴቶች በስታዲየሙ ውስጥ እና ዙሪያው ላይ ደስታቸውን ሲገልፁም ተስተውለዋል።
እዚህ ጋር ግን አንድ ነገር፤ ስታዲየም ለመግባት ከተመረጡት ውስጥ በርከት ያሉት የትዳር አጋሮቻቸው ኳስ ተጨዋች የሆኑ ናችው መባሉን DW አስነብብቧል።
የምትወደውን እግርኳስ ለመታደም ሜዳ የተገኘችው ፍሪዴ ፔይካር ስሜቷን እንዲህ ገልፃለች፦
“ቤተሰቦቼ ለእግር ኳስ ያለኝን ስሜት ያከብሩልኛል። ወደ ስታዲየም በመግባቴም ሁሉም ተደስተዋል”
በ1971 ዓ.ም. በኢራን የመጣውን እኢስላማዊ አቢዮት ተከትሎ የሀገሬው ሴቶች በአደባባዮች እና በስታዲየሞች ውስጥ እንዳይታዩ ህግ ተደነገገ።
ከዚያን ግዜ አንስቶ ሴቶች ጨዋታው ሲተላለፍ በቤታቸው ውስጥ በቴሌቪዥኖቻቸው ብቻ ተመልካቾች ሆነው ቀሩ።
ታዲያ የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ አስተዳዳሪ ፊፋ ባደረግው ጫና ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ጥቂት የሚባሉ ሴቶች በብሔራዊ ብድናቸው ጨዋታዎች ላይ ብቻ እንዲታደሙ ፍቃድ ተሰጥቷቸው ነበር።
በሳምሶን ገድሉ
2022-09-01
