የኤቲኤም ማሽን የባንክ ዘርፉን በትልቁ የለወጠ የቴክኖሎጂ ውጤት ነው። መሰረታዊ የገንዘብ ልውውጦችን ለማካሄድ ወደ ባንክ መሄድን በማስቀረት ዘርፉን ቀይሮታል። ዛሬ ላይ በመላው ዓለም ተደራሽነቱ እየሰፋም ይገኛል።
ወደ ታሪክ መለስ ስንል ኤቲኤም ማሽን ለመጀመሪያ ጊዜ ለተገልጋዮች አገልግሎት መስጠት የጀመረው ከ53 ዓመታት በፊት በዛሬዋ ዕለት ነበር። የዕለቱን ከታሪክ ትኩረታችን ነው።
ዛሬ ላይ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ከ4 ሚሊዮን የሚልቁ ኤቲኤም ማሽኖች አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው። አውቶሜትድ ቴለር ማሽን(Automated Teller Machine) የተሰኘ ስያሜ ያላቸው እነዚህ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የዓለምን የባንክ አገልግሎት ሁኔታንም እየቀየሩት ይገኛሉ።
53 ዓመታትን መለስ ስንል ታዲያ የመጀመሪያው ኤቲኤም ማሽን ለደንበኞች አገልግሎት እንዲውል የተደረገው በ1961 ዓ.ም. በዛሬዋ ዕለት ነበር።
ይሄው የመጀመሪያው ለህዝብ አገልግሎት ይፋ የሆነው ኤቲኤም አገልግሎት ላይ የዋለው በአሜሪካ፣ ኒውዮርክ፣ ሮክቫይል ሴንተር በተባለ ስፍራ በኬሚካል ባንክ ነበር።
በ1961 ዓ.ም. በኬሚካል ባንክ ለደንበኞች ገንዘብ የናስተላለፍ አገልግሎት መስጠትን ኤቲኤም ከጀመረ በኋላ ወደ ባንክ የመሄድ አስፈልጊነትን መቀነስ እንደሚያስችል አሳይቷል። ከዚያ በኋላም በባንክ ኢንዱስትሪው ላይ የሚታይ ለውጥ ማምጣት ችሏል።
ከአስርት ዓመታት በኋላ ደግሞ በ1970ዎቹ ይሄው የገንዘብ ማሽን በሰፊው በህዝብ ተወዳጅ መሆን ጀመሯል። ቀደም ብለው በሰው ገንዘብ ከፋይ ባለሙያዎች ይከናወኑ የነበሩ የገንዘብ መቀበል እና ማስተላለፍ አገልግሎቶችን በመተካት አገልግሎቶችን መስጠት ጀመረዋል። እንደዛሬው ግን በሰፊው ተደራሽ አልሆኑም ነበር።
የአውቶሜትድ ቴለር ማሽን (ATM) በዩናይትድ ስቴትስ በኬሚካል ባንክ ለደንበኞች አገልግሎት መስጠት ከመጀመሩ አስቀድሞ በሌሎችም አገሮች ቢሆን ገንዘብ ከፋይ ማሽንን ለመስራት የሚታገሉ ሰዎች ነበሩ።
በአሜሪካ ዶከትል የተባለ የዳላስ ኩባንያ ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ዶን ዌትዜል የዘመናዊው ኤ ቲ ኤም ሐሳብን እንዳመነጨ ይነገርለታል። ቬትዜል ይህን ጽንሰ ሐሳብ ያመነጨው በአንድ ባንክ ውስጥ አገልግሎት ለማግኘት ተሰልፎ እየጠበቀ እንደሆነ ይነገራል።
ለዚህም ችግር የመፍትሄ መመልከቻ እንደሚሆንም አሳይቷል። ይሄው ሃሳቡ ቀደም ብሎ የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚዎች አገልግሎት ለማግኘት የሚሰለፉትን ሰልፍ የሚቀይር ማሽን እንዲሰራ ምክንያት ሆኗል። እንደአሁኖቹ ኤቲኤም ማሽኖች ካርዶችን የሚጠቀምም ነበር።
በ1961 ዓ.ም. በኒው ዮርክ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ኤ ቲ ኤም ገንዘብ መስጠት ብቻ ነበር አገልግሎቱ፤ ሆኖም ከዓመት በኋላ የደንበኞችን ቀሪ ሂሳብን ማስታወቅን ጨምሮ የተለያዩ ተግባሮችን ማከናወን የሚችል ኤ ቲ ኤም አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።
በ1980ዎቹ ባንኮች ኤቲኤም ማሽኖችን ለሚጠቀሙ ደንበኞቻቸው ክፍያዎችን እስከመስጠት ደርሰው ነበር። የኤቲኤም ወንጀሎችም ተበራከቱ። ዘራፊዎች በቂ ብርሃን በሌለበት አካባቢ ኤቲኤም የሚጠቀሙ ሰዎችን ማጥመድ ጀመሩ።
ይባስ ብሎም የደንበኞችን የአገልግሎት ማግኛ ቁጥር ማወቅ የሚያስችላቸውን ሃሰተኛ ኤቲኤም መጠቀም ጀመሩ። ለዚህም ከተሞች እና የየክልል አስተዳዳሪዎች ኤቲኤም ማሽኖች ካሜራ እና የደህንነት ቁልፍ ያላቸው እንዲሆኑ የሚያስገድድ ህግ ለማውጣት ተገደዋል።
ዛሬ ላይ ኤቲኤም ማሽኖች የዓለማችንን የባንክ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ቀይረውታል። ከ53 ዓመታት በኋላ ቁጥራቸው 4 ሚሊዮንም ደርሷል።
በአብርሃም በለጠ
2022-09-02
