ሀገሬ ቲቪ

ቻይና ለዓሶች የኮቪድ ቫይረስ ምርመራ እያደረገች ነው

ዓለምን ብሙሉ በአንድ አይነት ገመድ ያሰረ፤ ሁሉንም በአንድ የያዘ ነው ኮቪድ 19። በእኛም ሀገር ቢሆን ኮቪድ ታየ ከተባለበት ግዜ አንስቶ በርካታ የጥንቃቄ መንገዶች ሲተገበሩም ቆይተዋል ምንም እንኳን አሁን አሁን ቢረሱም።

በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 600 ሚሊዮንን መሻገሩን ሁሉም ይወቅልኝ ሲል የዓለም የጤና ድርጅት WHO መረጃውን አጋርቷል።

በዚህ ቫይረስ ሳቢያ የተመዘገበው ሞትም 6 ሚሊዮንን እንደተሻገረ የጤና ድርጅቱ ጨምሮ ጠቁሟል። መቼም ስለ ኮቪድ ሲነሳ ቫይረሱ ከሰዎች ባለፈ በእንስሳቱም ላይ ይታያል ሲሉ ተመራማሪዎች ነግረውን ነበር።

ጠፍቷል በሚል ዓለም የተዘናጋበት ይህ ቫይረስ ዛሬም ለሰዎች ሞት እና መከራ ምክንያት ነው። ታዲያ አሁን ከወደ ቻይና የሰማነው ነገር ትንሽ የዚህን ቫይረስ አሳሳቢነት የሚያጎላው ሳይሆን አይቀርም።

ሀገሪቱ ከሰዎቹም አልፋ የባህር ፍጥረታቱን የኮቪድ ምርመራ እያደረገችላቸው እንደሆነ ተሰምቷል። የዚሁ ቫይረስ መነሻ ናት የምትባለዋ ቻይና ለበርካታ ወራቶች ዋነኛ የንግድ ማዕከል የሆኑ ከተማዎቿን ጭምር ዘግታ እንደነበር አይዘነጋም።

ያገረሸው የዚህ ቫይረስ ነገር ቻይናን ዳግም ወደ ጥብቅ ህጎቿ እንድትመለስ እያደረጋት ነው። በባህር ዳርቻከተማዋ ዢአሜን 40 የሚሆኑ ሰዎች ላይ ቫይረሱ በመገኘቱ ሳቢያ በከተማዋ የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የኮቪድ ምርመራን እንዲያደርጉም አዛለች።

ትዕዛዙ ግን ለሰዎች ብቻም አይደለም በዚህች ከተማ በስፋት ለምግብነት የሚውሉ የባህር ፍጥረታት እንደ ዓሳ ያሉቱ እንዲመረመሩም የሚል ነው ተብሏል።

በወደቧ ከተማ በርካታ ዓሳ አስጋሪዎች ይኖራሉ። ከባለፉት ወራት አንስቶ በዚህች ከተማ በኮቪድ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ስለመሆኑ ያሳያሉ።

በዚህ ስጋት የገባቸው የከተማው ባለስልጣናት የቫይረሱ መስፋት ምክንያቶች ዓሳ አጥማጆቹ ሳይሆኑ እንደማይቀሩ ይገምታሉ። የቫይረሱ መነሻ በህይወት ያለች ፍጥረት እና የአሳ ገበያ መሆኑ ደግሞ የባለስጣኑን ጥርጣሬ ከፍ ያደርገዋል።

አሁን ታዲያ በቻይና ዓሳዎች በህይወት እያሉ የኮቪድ ምርመራን እያደረጉ ይገኛሉ። አሳዎቹ በህይወት እያሉ ከአፋቸው ውስጥ ናሙናዎች ሲወሰዱ የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች በሚዲያዎች ላይ ከተለቀቀ በኋላ በርካቶችን ወይ ጉድ አሰኝቷል።

የዜሮ ኮቪድ ፖሊሲን እየተከተለች ያለችው ቻይና በሀገሯ የቫይረሱን ለማጥፋት በርካታ ስራዎችን እየሰራች ትገኛለች። ይህንን እቅዷን ለማሳካትም ከሀገሯ ዜጎች በተጨማሪ በዱር አራዊት ፓርክ ውስጥ ያሉ እንስሳቶቿን ሁሉ የቫይረሱን ምርመራ አድርጋላቸው እንደነበር አይዘነጋም ሲል ቢቢሲ አስነብቧል።

በሳምሶን ገድሉ
2022-09-02