የባንክ ዘርፍን ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት የማድረግ ውሳኔ የኢትዮጵያ ባንኮች ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ዕድል እንደሚፈጥር ተገለጸ። ይህንን የገለጹት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቤ ሳኖ ናቸው።
የባንኩ ዘርፍ ለዓለም ገበያ በሩን ሙሉ በሙሉ ዝግ አድርጎ መቆየቱ በሀገር ውስጥ ባንኮች ዕድገት ላይ ያሳደረው ጫና ቀላል አይደለም ያሉት ፕሬዝዳንቱ የባንክ አገልግሎቱን ድንገት ለዓለም ገበያ ወለል አድርጎ መክፈትም አደጋ ስለሚኖረው በሚዛኑ ማስኬድ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባካሄደው 13ኛ መደበኛ ስብሰባው የባንክ ዘርፍን ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት ለማድረግ የቀረበ ረቂቅ ፖሊሲ በሥራ ላይ እንዲውል ከቀናት በፊት ወስኗል።
ስለ ውሳኔው አስተያየት የሰጡት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ የባንኩ ዘርፍ ለዓለም ገበያ ዝግ ሆኖ መቆየቱ የሀገር ውስጥ ባንኮችን እድገት እንዳቀጨጨው ተናግረዋል።
በሌላ በኩል የሀገር ውስጥ ባንኮች በውድድሩ ተጎጅ እንዳይሆኑም የውጭ ባንኮች በተወሰነ የአክስዮን ድርሻ ገብተው ቀስ በቀስ ድርሻቸውን እንዲያሳድጉ ማድረግ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
የውጪ ኢንቨስተሮች በባንክ ዘርፍ እንዲሰማሩ ማድረግ ዓለም አቀፍ ልምድ በሌላቸው የሀገር ውስጥ ባንኮች ተገድቦ የነበረውን ደካማ ውድድር በማስቀረት አብሮ የመስራት ትልቅ አቅም እንደሚፈጥርም ገልጸዋል።
የባንኩ ዘርፍ ለዓለም ገበያ ክፍት መደረጉ የሚበረታታ ቢሆንም በጥንቃቄ መመራት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
በብሩክ ያሬድ
2022-09-05
