በአማራ ክልል ሁሉም የመንግሥት ተቋማት መደበኛ አገልግሎት መስጠት ጀመሩ፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለዉን ጦርነት ተከትሎ የቀረበውን የህልውና ትግል ጥሪ ለመደገፍ መደበኛ አገልግሎት አቋርጠው የነበሩ ተቋማት ናቸው ወደ ስራ የተመለሱት ፡፡ የአማራ ክልል መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት አሁን ላይ የህልውና ዘመቻው መልክ እየያዘ ስለሆነና አብዛኞቹ ቦታዎችም ከጦርነት ነጻ ስለወጡ ወደ ስራ ተመልሰዋል ብለዋል፡፡ አቶ ግዛቸው እንደገለጹት ውሳኔው ታሳቢ ያደረገው ሌሎች ሥራዎች እንዳይጎዱና ኢኮኖሚውም እንዳይቀዛቀዝ በሚል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ኃላፊው ሁሉም የመንግሥት ተቋማትና ሠራተኞች ከመደበኛ ተግባራቸው ጎን ለጎን የህልውና ዘመቻውን መደገፍ ይቀጥላሉ ብለዋል፡፡ ሁሉም ተቋማት መደበኛ አገልግሎታቸውን ለደንበኞቻቸው እንዲሰጡም ለክልሉ መንግስት ሰራተኞች ጥሪ ቀርቧል፡፡ የ ክልሉ መንግሥት በሕወሓት ቡድን ተይዘው የቆዩ አካባቢዎች ብዙ ነገራቸው የተጎዳ በመሆኑ ሠራተኞች ጉዳቱን ሊያካክስ በሚችል ሞራልና ተነሳሽነት ሥራ ጀመረዋል ብሏል፡፡
በሀገሬ ቲቪ
2021-12-29
