ሀገሬ ቲቪ

ጀርመን የነዳጅ ውድነትን ለመቋቋም 65 ቢሊዮን ዩሮ መደበች

ከጊዜ ወደ ጊዜ የነዳጅ ዋጋ እየናረ እና ሀገራትን እየፈተነ ያለ ምርት ኾኗል። የበርካታ ሀገራትን የነዳጅ ቋት የምትሞላው ሩሲያ ከዩክሬን ጋር ጦርነት ውስጥ መግባቷ ደግሞ ጦሱ ለበርካታ ሀገራት ተርፏል።

በዚህ ጉዳይ እየተዋከቡ ከሚገኙ ሀገራት መካከል ጀምርመን ችግሩን ለማቅለል እና ለመቋቋም 65 ቢሊዮን ዩሮ መድቢያለሁ ብላለች። ይህ ውሳኔዋ የተሰማው ደግሞ ከኹለት ቀናት በፊት ሩሲያ ውደ ጀርመን የተዘረጋውን ኖርድ 1 የተሰኘው ጋዝ ማስተላለፊ መሥመር ለጥገና በሚል ሰበብ ከዘጋች በኋላ ነው።

ከ3 ቀነት በኋላ እከፍተዋለው ያለችን መስመር ላልተወሰነ ቀን እንደማትከፍተውም አሳውቃለች። የጀርመን መንግሥት በጉዳዩ ላይ በሰጠው ገለጻ በነዳጅ ውድነት አሊያም በኀይል አቅርቦት ችግር ሕዝባችና እና የንግድ ተቋማት ፈተና ውስጥ እንዳይገቡ እና በሕዝብ ትራንስፖርት ላይ ያለውን ድጎማ ለመደገፍ ሲባል 65 ቢሊዮን ዩሮ መበጀት እንዳስፈለገ አስታውቋል።

በተለይም አውሮፓን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት ወደ ክረምት እያመሩ መኾናቸውን ተከትሎ የኃይል ፍላጎት ከምንግዜውም በላይ የሚጨምርበት ወቅት ነው።

ይህንንም ከግንዛቤ በማስገባት የአውሮፓ ሀገራት የተለየዩ እርምጃዎችን እየወሰዱ ይገኛሉ። ጀርመንም ይህን ጉዳይ ከግምት ውስጥ አስገብቼ የተለያዩ ሥራዎችን እየሰራኹ ነው ብላለች።

በመጪው ታህሳስ ወር ከሩሲያ የምታስገባውን የተፈጥሮ ጋዝ ሙሉለሙሉ ለማቋረጥም ዕቅድ መያዟን የጀርመን ቻንስለር የኾኑት ኡላፍ ሆልዝ ተናግረዋል። ሩሲያ አታዋጣንም፤ ታማኝ የኃይል ወዳጅ አይደለችም ሲሉም ሩሲያን ወርፈዋታል።

መንግስታቸው የተቻለውን ኹሉ እያደረገም እንደኾነ ተናግረዋል። ኹሉንም ነገር በጋራ ማድረግ ከቻልን ስለ 65 ቢሊዮን ዩሮ ገንዘብ ማውራት ያስችለናል። ይህም አስፈላጊ የኾነውን ነገር በሰፊው እንዳደረግን አመላካች ነው።

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮለድሚር ዘለንስኪም በበኩላቸው ሩሲያ ኖርድ 1 የተሰኘው ጋዝ ማስተላለፊ መሥመር መዝጋቷ መጪው የክረምት ወር ለአውሮፓውያን ከባድ ሊኾንባቸው ይችላል ማለታቸውን አልጀዚራ ዘግቧል። በክረምቱ ወራት እነዚኹ ሀገራት በነዳጅ እጥረት እንዲታመሱ ለማድረግ የአውሮፓ ዜጎችን መደበኛ ሕይወት ለማጥፋት ሩሲያ ተዘጋጅታለች ሲሉም ዘለንስኪ ተነግረዋል።

በሰሜን ምስራቅ ጀርመን ማለትም የኖርድ 1 ጋዝ ማስተላለፊያ በሚገኝበት አካባቢ ተቃውሞ የሚያሰሙ ጀርመናውያን ተሰብስበው እንደነበር ቢቢሲ ዘግቧል። የነዳጅ ዋጋ የሚቀመስ አልኾን ብሎናል ያሉ ዜጎች ናቸው በቦታው ተሰብስበው የነበሩት። በጀምርመን መንግሥት ተዘግቶ ያለውን የኖርድ 2 ጋዝ ማስተላለፊያ መስመር እንዲከፈትም ሲጠይቁ ነበር ተብሏል።

ጀርመን አሁን ከገባችበት አጣብቂኝ ውስጥ ለመውጣት ትረቷን እንዳላቋረጠች ገልጻለች በንዳጅ ምርት የሩሲያ ጥገኛ ኾኜ አልቆይም ወደሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ፌቴን ማዞሬ የማይቀር ነው ማለቷ የሚታወስ ነው።

በሙሉጌታ በላይ
2022-09-05