ሀገሬ ቲቪ

ገጣሚው እና የመጀመሪያው የሴኔጋል ፕሬዝዳንት

የ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ብዙ የአፍሪካ ሀገራት ነጻ የወጡበት ነው። በአፍሪካዊነት ስሜቱ በስነጽሁፍ ስራዎቹ በማንጸባረቅ ስማቸው የሚነሳ መሪም ናቸው። ሊዮፖልድ ሴዳር ሴንጎር። እኒህ ሰው የመጀመሪያው የምዕራብ አፍሪካዊቷ ሃገር ሴኔጋል ፕሬዝዳንት ሆነው የተመረጡት በዛሬዋ ዕለት በ1952 ዓ.ም. ነበር። የዕለቱን ከታሪክ ትኩረታችን ነው።

ገጣሚ እና ባለቅኔ፣ መምህር እና የፖለቲካ ሰው፣ የመጀመሪያው የሴኔጋል ፕሬዝዳንት እና የጥቁርነት ጽንሰ ሃሳብ አቀንቃኝ የሆኑት በሙሉ ስማቸው ሊዮፖልድ ሴዳር ሴንጎር የተወለዱት በ1889 ዓ.ም. የፈረንሳይ ምዕራብ አፍሪካ ተብላ በምትጠራዋ በአሁኗ ሴኔጋል ጆል ነበር።

የነጋዴ ባለጸጋ ልጅ የነበሩት ሴንጎር በአቅራቢያቸው ካለ የካቶሊክ ሚሽን ትምህርት ቤት ተምረዋል። በ20 ዓመታቸውም ወደ ዋና ከተማዋ ዳካር በመጓዝ በሊሴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን ተከታትለዋል።

በ1920ዎቹ ሴንጎር በከፊል የነፃ ትምህርት ዕድል አግኝተው ወደ ፓሪስ በመሄድ በሊሴ ሉዊ-ለ-ግራንድ እና በሶርቦን ከተማ መደበኛ ትምህርታቸውን ቀጠሉ።

በነዚህ ዓመታት ሴንጎር በዘመናዊ ስዕል፣ ቅርፅ እና ሙዚቃ ላይ የአፍሪካን የኪነ-ጥበብ አሻራ በማያሻማ ሁኔታ ተገንዝበዋል።። አፍሪካ ለዘመናዊ ባህል ልታበረክተው የምትችለው አቅሟ ላይም እምነት አሳድረዋል።

በ1920ዎቹ መጨረሻ በፈረንሳይ የትምህርት ስርዓት ውስጥ ሴንጎር የመጀመሪያው ከፍተኛ ደረጃ ያለው መምህር ነው። በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና በዩኒቨርሲቲ ደረጃ የማስተማር ፍቃድም ነበራቸው። ኋላም የአፍሪካ ቋንቋዎች እና ስልጣኔ ፕሮፌሰር ሆነዋል።

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጀመሪያ ተመልምለው የነበሩት ሴንጎር ተይዘው በናዚ ማጎሪያ ካምፖች ለሁለት ዓመታት ያክል ቆይተዋል። በዚያም አንዳንድ ምርጥ ግጥሞቻቸውን ጽፈዋል። ከእስር ከወጡ በኋላ በፈረንሳይ የተቃውሞ ቡድንን ተቀላቅለዋል።

ከጦርነቱ በኋላ ሴንግሆር የፈረንሳይ ጠቅላላ ጉባኤ አባል ሆኑ። ከሴኔጋል ሁለት ኃላፊዎች አንዱ በመሆን ፓሪስ ውስጥ ወደ ብሔራዊ ጉባኤ ተልከዋል።

በ1940 ዓ.ም. የሴኔጋል ዴሞክራቲክ ብሎክን የመሰረቱ ሲሆን፣ የዚያ ፓርቲ እጩ እንደመሆናቸው መጠን በ1943 ዓ.ም. ለፈረንሳይ ብሔራዊ ምክር ቤት በተደረገው ምርጫ በሰፊ ድምጽ ዳግም ተመረጠዋል። ከአምስት ዓመት በኋላም የሴኔጋል የባቡር ሐዲድ ማዕከል የቲዬ ከንቲባ በመሆን በድጋሜም ምክትል ሆነው ተመረጠዋል።

የፈረንሳይ የምዕራብ አፍሪካ ቅኝ ግዛቶች ነፃነት ለማግኘት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጋደሉ መጥተዋል። የፈረንሳዩ ፓርላማ ለአፍሪካ ክልሎች ከፍተኛ የሆነ የራስ ገዝ አስተዳደር ይሰጥ የነበረው የሎይ ካድሬ ህግ ሲፀና ሴንጎር ድርጊቱን ከተቃወሙት መካከል አንዱ ነበሩ። ምክንያቱም ከፌደራል መንግስት ይልቅ ለክልሎች ትኩረት መስጠቱ ትናንሽና የተበታተኑ ሀገሮች እንዲበራከቱ ያደርጋል የሚል ስሜት ስላደረበት ነው።

ሴንጎር ይህን ድርጊት ለመቃወም በፈረንሳዩ ኢኳቶሪያል አፍሪካና በፈረንሳይ ምዕራብ አፍሪካ መካከል ኅብረት በመመሥረት ረድተዋል። ይህ ኅብረት በ1951 ዓ.ም. ለአጭር ጊዜ የቆየው የማሊ ፌዴሬሽን እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል። በዚህ ምድብ ሴኔጋል፣የፈረንሳይ ሱዳን ተብላ የምትጠራዋ ማሊ፣ ከዳሆሚ (ቤኒን) እና ላይኛው ቮልታ (ቡርኪና ፋሶ) አባል ነበሩ።

በዚያው ዓመት ለፈረንሳይ የነጻነት ጥያቄን ካቀረቡ በኋላ የማሊ ፌደሬሽን መቆየት የቻለው ለጥቂት ጊዜ ነበር። የፈረንሳይ ሱዳን ማሊ እና ሴኔጋል ከተነጣጠሉ በኋላ ለየብቻቸው ነጻነታቸውን አግኝተዋል። ሊዮፖልድ ሴንጎርም በ1952 ዓ.ም. የመጀመሪያው የሴኔጋል ፕሬዝዳንት ሆነዋል።

ከሁለት ዓመታት በኋላ መፈንቅለ መንግስት ቢሞከርባቸውን ህዝብ ከርሳቸው ጎን ቆሞላቸዋል። ኋላም በድጋሜ ተመርጠው በፕሬዝዳንትነት ካገለገሉ በኋላ በ1972 ዓ.ም. ከስልጣን ጡረታ ወጥተዋል። በፈቃደኝነት ስልጣናቸውን በመልቀቅም የመጀመሪያው የአፍሪካ ፕሬዝዳንት ሆነዋል። ለተከታያቸው አብዱ ድዮፍም በሰላም ስልጣናቸውን አስረክበዋል።

በስልጣን ዘመናቸው የሴኔጋልን ግብርና ለማዘመን የሰሩ ሲሆን ለሶስተኛው ዓለም ሞጋች ተናጋሪም ነበሩ፤ አፍሪካን የጎዳውን ኢፍትሃዊ የሆነ የዓለም ንግድን ይተቹ የነበሩት ሴንጎር ዲሞክራቲክ ሶሻሊዝምን ያቀነቅኑ ነበር።

ጥቁርነትን የሚያቀነቅነውን አፍሪካዊነት ላይ የሚያተኩር የስነ ጽሁፍ ጽንሰሃሳብን በማቀንቀንም ከቀዳሚዎቹ ናቸው። መምህር፣ የጽነ ጽሁፍ ሰው- ገጣሚ፣ የአፍሪካዊነት አቀንቃኝ እና የፖለቲካ ሰው የነበሩት ሴንጎር በ1994 ዓ.ም. አርፈዋል።

በአብርሃም በለጠ
2022-09-05